በከተሞች የሚስተዋሉ የሌብነትና የመልካም አስተዳደር ችግሮችን መቀረፍ የሚቻለው በህብረተሰቡ ትብብር ነው – ዶክተር አበባየሁ ታደሰ

በከተሞች የሚስተዋሉ የሌብነትና የመልካም አስተዳደር ችግሮችን መቀረፍ የሚቻለው በህብረተሰቡ ትብብር ነው – ዶክተር አበባየሁ ታደሰ

ሀዋሳ፡ ጥር 08/2016 ዓ.ም (ደሬቴድ) በከተሞች የሚስተዋሉ የሌብነትና የመልካም አስተዳደር ችግሮችን መቀረፍ የሚቻለው በህብረተሰቡ ትብብር እንደሆነ በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የማህበራዊ ክላስተር አስተባባሪና የትምህርት ቢሮ ሀላፊ ዶክተር አበባየሁ ታደሰ ገለጹ፡፡

በሶዶ ከተማ የተካሄደው የከተማ አቀፍ ህዝባዊ ኮንፈረንስ ተጠናቋል።

በመድረኩ ማጠቃለያ ላይ የተገኙት በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የማህበራዊ ክላስተር አስተባባሪና የትምህርት ቢሮ ሀላፊ ዶክተር አበባየሁ ታደሰ እንደገለፁት ለከተሞች ለውጥና ዕድገት የነዋሪዎች ሚና መተኪያ የሌለው ነው።

በከተሞች አከባቢ የሚስተዋሉ የሌብነትና የመልካም አስተዳደር ችግሮች በመንግሥትና በህብረተሰቡ ትብብር መቀረፍ እንዳለባቸውም አሳስበዋል።

በከተሞች ያሉ የመልካም አሰተዳደር ችግሮችን ለመቅረፍ እና የከተሞችን ዕድገት ለማፋጠን በየ3 ወሩ ከተማ አቀፍ ህዝባዊ ጉባኤዎችን በክልሉ ከተሞች ለማካሄድ መታቀዱንም ይፋ አድርገዋል ዶክተር አበባየሁ።

በመድረኩ የተሳተፉት የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ለከተማዋ ሁለንተናዊ ለውጥ ከመንግሥት ጋር በጋራ እንሰራለን በማለት አረጋግጠዋል።

የሶዶ ከተማ ያላት ፀጋ ትልቅ መሆኑን ያነሱት የከተማዋ ነዋሪዎች ይሄን ዕድል በአግባቡ ልንጠቀምበት ይገባልም ብለዋል።

መንግሥትም ያሉበትን ክፍተቶች ማስተካከል አለበት ነው ያሉት የከተማዋ ነዋሪዎች።

ሌብነትና ስርቆት፣ በዘመድ አዝማድ መቀጠር፣ ህገ ወጥ የመሬት ወረራና የፕላን ጥሰት፣ የመፈጸም አቅም ውስንነት ያለባቸው ግለሰቦችን በመንግሥት የስራ ሀላፊነት ቦታ ላይ ማስቀመጥና ቀልጣፋ የመንግስት አገልግሎት አለማግኘት ችግሮች እንዲፈቱ የከተማዋ ነዋሪዎች ጠይቀዋል።

የወላይታ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ሳሙኤል ፎላ የሶዶ ከተማ በብዙ ፀጋዎች የተከበበች ከተማ ናት በማለት ይህን ፀጋ ወደመሬት በማውረድ ህብረተሰቡን መጥቀም ይገባል ብለዋል።

ከተማዋ ያላትን ፀጋ በሚገባ ደረጃ ባለመጠቀሟ በሚጠበቀው ልክ ወደፊት መራመድ አልቻለችም ብለዋል።

እነዚህን አደናቃፊ ተግዳሮቶች በጋራ መወጣት የሁላችንም ግዴታ ነውም ብለዋል።

ከተማ የሚያድገው በከተማዋ ነዋሪ ተሳትፎ ነው ያሉት አቶ ሳሙኤል በከተማዋ በሚደረጉ ልማታዊ እንቅስቃሴዎች ነዋሪዎች ንቁ ተሳትፎ ማድረግ አለባቸው ነው ያሉት።

ማዘጋጃ ቤታዊ አገልግሎቶች ለበርካታ አመታት የመልካም አስተዳደር ችግር ምንጮች እየሆኑ መቆየታቸው የተነሳ ሲሆን ይህም በጋራ ትብብር መቀረፍ አለበት ተብሏል።

በከተማዋ ያሉ ዘርፈ ብዙ ችግሮችን በአጭር ጊዜ ውስጥ ዜሮ ማድረስ ይቻል ዘንድ አቶ ሳሙኤል የህብረተሰቡን ያላሰለሰ ድጋፍ ጠይቀዋል።

ከከተማዋ የሚመነጨውን ገቢ ከፍ በማድረግ ለከተማዋ ልማት አወንታዊ ሚና በመጫወት ብልሹ አሰራርንም በጋራ እንመክትም ብለዋል።

ዘጋቢ፡ ጀማል የሱፍ