ግማደ መስቀሉ የተገኘበት ዕለት

ግማደ መስቀሉ የተገኘበት ዕለት

ከመስቀል በዓል ጋር ተያይዞ ከሃይማኖት አስተምህሮ እና ከታሪክ አንፃር የሚነገሩ እና የተፃፉ መረጃዎች በተለያየ መንገድ ተሰንደው ይገኛሉ፡፡ በዚህም ታሪክ እንደሚያስረዳው በሦስተኛው መቶ ክፍለ ዘመን በሮም ግዛት እየተዳከመ የሔደውን የክርስትናን እምነት ለመጠበቅ ነበር የሀገሪቱ ንግሥት ዕሌኒ ልጇን ቆስጠንጢኖስን ከልጅነቱ ጀምሮ ስለ ክርስትና ሃይማኖትና ስለ ክርስቲያኖች መከራ ስታስተምረው እንደ ነበር ይነገራል፡፡

ይህም በእርሱ ላይ ስለ ክርስትና እንዲሁም ስለ ክርስቲያኖች በጎ አመለካከትን ፤ ንጉሡም በሮም ከነገሡት ቄሣሮች በተሻለ መንገድ ክርስትናን እንዲቀበል አደረገው፡፡

በዚያን ግዜ ንጉሱ ለመጀመሪያ ጊዜ ነው ዐዋጅ ያወጀው፤ ከዚህም በኋላ ክርስትና ብሔራዊ ሀይማኖት ሆነ፡፡ በሦስት መቶ ሃያ ሰባት ዓ.ም ንግሥት ዕሌኒ መስቀሉን ከተቀበረበት ቦታ ፈልጋ በማግኘት ወደ ኢየሩሳሌም እንደተጓዘች የታሪክ መፅሀፍት ይጠቅሳሉ፡፡ ይህንንም አንዲያሳካላት ፈጣሪዋን ለመነችው፤ ሥእለትም እንደተሳለች ይነገራል፡፡

ከዚህ በኋላ ግማደ መስቀሉን ለማግኘት እንዲያመቻት ቅድስት ዕሌኒ ወደ ኢየሩሳሌም ከተጓዘች በኋላ ስለ መስቀል ለማወቅ መረመረች፤ ጠየቀችም፤ ሆኖም ያለበትን ቦታ የሚነግራት ሰውማግኘት አልቻለችም፡፡ተስፋ ሳትቆርጥ ተግታ በመፈለጓ አንድ ኪራኮስ የተባለ አረጋዊ የጎልጎታን ኮረብታ ሊያሳያት ችሏል፤ ነገር ግን ከሦስቱ ተራሮች መካከል መስቀሉ የሚገኝበትን ለይቶ ለማወቅ ባለመቻሉ ንግሥት ዕሌኒ ወደ አምለኳ እንደጸለየች የሀይማኖቱ አስተምህሮ ይገልፃል፡፡

ከሦስቱ ተራሮች የቱ እንደሆነ ለመለየት በእግዚአብሔር መልአክ ርዳታ ደመራ አስደምራ ብዙ እጣንም በመጨመርና በማቃጠልም ጸሎት ተደረገ፡፡ በዚህ ጊዜ የእጣኑ ጢስ ወደ ሰማይ በመውጣት በቀጥታ ተመልሶ መስቀሉ ባለበት ተራራ ላይ በማረፍና በመስገድ መስቀሉ ያለበትን ትክክለኛ ስፍራ አመለከታት፡፡ የእግዚአብሔር ድንቅ ሥራም በዚህ ተገለጸ፡፡

የኢትዮጵያ ቤተክርስቲያን የምትፈልገው ኢየሱስ ክርስቶስ የተሰቀለበትን መስቀሉን እንጂ ወርቅ ስላልነበረ ንጉሥ ዳግማዊ ዳዊት ይህን ገለጹላቸው:: በመሆኑም የግብፅ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን ግማደ መስቀሉን ከሌሎች ንዋየ ቅድሳት ጋር ለኢትዮጵያ ሰጠች::

ግማደ መስቀሉም በግሸን ማርያም ገዳም በእግዚአብሔር አብ ቤተክርስቲያን ይገኛል:: መስቀሉን ለመዘከርም የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን መስከረም ፲፮ እና መስከረም ፲፯ ቀን ደምራ ጸሎትና ምሥጋና ታቀርባለች።

ደመራ ደምሮ በጢሱ አመላካችነት መስከረም 17 ቀን ቁፋሮ ተጀምሮ መጋቢት 10 ቀን መስቀሉ እንደተገኘ በሃይማኖቱ አስተምህሮ ይነገራል፡፡ መጋቢት 10 ቀን የዐብይ ፆም ወራት በመሆኑ አባቶች መስቀል በዓልን ቁፋሮ በተጀመረበት እንዲከበር ስርዓትን ሰርተው ባለፉት መሰረት መስከረም 17 ተከብሮ ይውላል፡፡

አዘጋጅ፡ ቤተልሔም ለገሠ