በቡታጅራ ከተማ ቢሮዎች ዝግጁ ሆነዋል

በቡታጅራ ከተማ ቢሮዎች ዝግጁ ሆነዋል

ሀዋሳ: ጳጉሜ 03/2015 ዓ.ም (ደሬቴድ) በቡታጅራ ከተማ የተመደቡ ክላስተር መሥሪያ ቤቶች የቢሮ ዝግጅት መደረጉን የጉራጌ ዞን ምክትል አስተዳዳሪ አቶ ሙስጠፋ ሀሰን ገለፁ::

ጳጉሜ 04 ቀን 2015 ዓ.ም የሥራ ማስጀመሪያ መርሀግብር እንደሚከናወንም ተገልጿል::

የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የማዕከል ከተማ ከሆኑት አንዷ የሆነችው የቡታጅራ ከተማ አስፈላጊ ቅድመ ዝግጅቶችን ማጠናቀቋን የጉራጌ ዞን ምክትል አስተዳዳሪ አቶ ሙስጠፋ ሀሰን ተናግረዋል::

ከደሬቴድ ጋር ቆይታ ያደረጉት ምክትል አስተዳዳሪው ከተማው የክላስተር ከተማ ሆና መመረጧ ዘርፈ ብዙ ጥቅሞች ያሉት ነው ብለዋል:: ይህም ከሥራ ዕድል ፈጠራ፣ ከገበያ ትስስር እና ከኢንቨስትመንት አንፃር ትልቅ አስተዋጽኦ ያበረክታል ነው ያሉት::

ከተማዋ ለእንግዶች ምቹ ትሆን ዘንድ ከከተማ ፅዳት ጀምሮ እስከ ቢሮ ዝግጅት ያሉ ተግባራት መከናወናቸውን አስታውቀዋል:: ይህን ተከትሎ ጳጉሜ 04 ቀን 2015 ዓ.ም ከፍተኛ የክልሉ የሥራ ኃላፊዎች በተገኙበት ይፋዊ የሥራ ማስጀመሪያ መርሀግብር ይካሄዳል::

የቢሮ ኃላፊዎች በቀጥታ ወደ ሥራ በመግባት የተሰጣቸውን የህዝብና የመንግስታ ኃላፊነት ያለምንም ችግር ይወጡ ዘንድ ምቹ ሁኔታዎችን የመፍጠር ሥራ መሠራቱን አቶ ሙስጠፋ ገልጸዋል::

ከከተማዋ ባለሀብቶች ጋር በመነጋገር ለኃላፊዎቹ ለ6 ወር በነፃ የሚኖሩበት የመኖሪያ ቤት ተዘጋጅቷል ብለዋል:: ባለሀብቱ ላሳየው በጎ ፈቃደኝነት ምስጋና አቅርበዋል::

ወደ ከተማዋ ተመድበው የሚመጡ የመንግስት ሠራተኞችም ባይተዋርነት ሳይሰማቸው እንደ ቤታቸው ሆነው እንዲኖሩ የሚያስችል ሥራ ከህብረተሰቡ ጋር ተሰርቷል ብለዋል::

እድገት በጊዜ ሂደት የሚመጣ መሆኑን ህብረተሰቡ ተገንዝቦ ለእንግዶች በተመጣጣኝ ዋጋ የመኖሪያ ቤት ማከራየት መልካም መሆኑን አንስተዋል::

በአራቱ ቢሮዎች ተመድበው ወደ ከተማዋ ለሚመጡ የመንግስት ሠራተኞች በማህበር በማደራጀት የመኖሪያ ቤት እድል ተጠቃሚ እንዲሆኑም ቅድሚያ ተሰጥቶ እንደሚሠራ አብራርተዋል::

ዘጋቢ: ማሬ ቃጦ