እየተጠናቀቀ በሚገኘው ዓመት የቱሪዝም ማረፊያዎችና መዳረሻዎችን በማልማት ተጨባጭ ውጤት መመዝገቡ ተገለጸ

እየተጠናቀቀ በሚገኘው ዓመት የቱሪዝም ማረፊያዎችና መዳረሻዎችን በማልማት ተጨባጭ ውጤት መመዝገቡ ተገለጸ

ሀዋሳ፡ ጳጉሜ 03/2015 ዓ.ም (ደሬቴድ) እየተጠናቀቀ በሚገኘው ዓመት የቱሪዝም ማረፊያዎችና መዳረሻዎችን በማልማት እንዲሁም በባህልና በስፖርት ዘርፍ በተከናወኑ ተግባራት ተጨባጭ ውጤት መመዝገቡን የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል የባህል፣ ቱሪዝምና ስፖርት ቢሮ አስታወቀ።

በ2016 ዓ.ም የክልሉን ገጽታ የበለጠ በማስተዋወቅ የኢኮኖሚ ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ እንደሚሠራም ተገልጿል።

የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል የባህል፣ ቱሪዝምና ስፖርት ቢሮ ኃላፊ አቶ ፋንታሁን ብላቴ በተለይ ለደቡብ ሬዲዮና ቴሌቪዥን ድርጅት ዋካ ቅርንጫፍ እንደገለጹት የክልሉን ሕዝቦች ባህላዊ እሴቶች፣ ታሪካዊና ተፈጥሯዊ መስህቦችን በመጠበቅና በማስጠበቅ፣ ቅርሶችን በማጥናት፣ በማልማት፣ በማስተዋወቅ እና የኢኮኖሚ ምንጭ እንዲሆኑ የሚያስችል ተግባር ቢሮው በቅንጅት እያከናወነ ይገኛል።

በክልሉ የነበረውን የኅብረተሰቡን አብሮ የመኖር፣ የመቻቻልና የመደጋገፍ ባህል ለማስቀጠልና እንዲጎለብት ለማድረግ የሚያስችሉ ተግባራት በትኩረት እየተከናወኑ ይገኛሉ።

በስፖርት ዘርፍ የባለድርሻ አካላት ተሳትፎ በላቀ ደረጃ በማሳደግ፣ ህዝባዊ መሠረት እንዲኖረውና መልካም ገጽታ በመገንባት የአገልግሎት አሰጣጥ ሥርዓት በማዘመን የወጣቶች ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ በማከናወን ላይ እንደሚገኝም አቶ ፋንታሁን ገልጸዋል።

በክልሉ የሚዛን አማን የስፖርት አካዳሚ የአፈጻጸም መምሪያ በማዘጋጀት ጤናማ፣ አምራች እና ንቁ ዜጋ ለማፍራት እንዲቻል ለተግባሩም ትኩረት መሰጠቱን ጠቁመዋል።

የቱሪዝም ክፍለ ኢኮኖሚን በማነቃቃት በኩል የገበታ ለሃገር ፕሮጀክት አካል የሆኑ የሃላላና የጨበራ ሎጆች፣ የዙላ ፓርክ፣ የከፋና የሸካ ጥብቅ ደኖች እንዲሁም በክልሉ 6 የዞን መዋቅሮች የሚገኙ 13ቱ ብሔረሰቦች የአለባበስ፣ የአመጋገብና የአጨፋፈር ባህሎች ክልሉን ለማስተዋወቅና ከፍተኛ ገቢ ለማግኘት የጎላ ሚና በመኖሩ የማልማትና የማስተዋወቅ ሥራ በትኩረት እየተሠራ ይገኛልም ብለዋል።

እየተጠናቀቀ በሚገኘው 2015 ዓ.ም ክልሉ አዲስ የተደራጀ ክልል ከመሆኑ ጋር ተያይዞ የሚታዩ ክፍተቶችን በመሸፈን፣ በቱሪስት መዳረሻዎች የአገልግሎት ሰጪ ተቋማት ግንባታ ችግር ያለበት በመሆኑ በመጪው ዓመት ችግሮቹን ለመፍታት እንደሚሠራም አስረድተዋል።

ወደ ክልሉ የሚመጡ የቱሪስቶች የቆይታ ጊዜ እንዲረዝም ለማስቻል በሆቴልና ቱሪዝም ዘርፍ የአልሚ ባለሃብቶችንና የህብረተሰቡን ድጋፍና ተሳትፎ ለማሳደግ ግብ ተጥሎ እየተሠራ እንደሚገኝም ኃላፊው ገልጸዋል።

ከባህል፣ ከቱሪዝም እና ከስፖርት ዘርፍ የክልሉን ብሎም የአገሪቱን ማኅበራዊና ምጣኔ ሃብታዊ ብልጽግና በዘላቂነት ማረጋገጥ ዓቢይ ተግባር በመሆኑ የባለድርሻ አካላት ድጋፍ ወሳኝ በመሆኑም፣ በተለይም አልሚ ባለሀብቶች፣ መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች እንዲሁም የምሁራን ድጋፍና በቅንጅት መስራት ተገቢ በመሆኑ ከሁሉም አካላት ጋር በቅንጅት ሊሠራ እንደሚገባም ጥሪ አቅርበዋል።

ዘጋቢ፡ መሣይ መሠለ – ከዋካ ጣቢያችን