የጋሞ ዞን ህዝብ ምክር ቤት አቶ አባይነህ አበራን የዞኑ ዋና አስተዳዳሪ አድርጎ ሾመ

የጋሞ ዞን ህዝብ ምክር ቤት አቶ አባይነህ አበራን የዞኑ ዋና አስተዳዳሪ አድርጎ ሾመ 

ሀዋሳ፡ ጳጉሜ 02/2015 ዓ.ም (ደሬቴድ) የጋሞ ዞን ህዝብ ምክር ቤት የዞኑን አስተዳዳሪ ሹመት አፀደቀ።

የጋሞ ዞን ህዝብ ምክር ቤት 4ኛ ዙር መርሀ ግብር 10ኛ አመት የስራ ዘመን 19ኛ መደበኛ ጉባኤ እየተካሄደ ይገኛል።

የምክር ቤት ዋና አፈ ጉባኤ ወ/ሪት አለሚቱ ዮሴፍ ባደረጉት የመክፈቻ ንግግር በበጀት አመቱ የህዝቡን የልማትና የመልካም አስተዳደር ችግሮችን ለመፍታት አቅምን በማቀናጀት ሰፊ ርብርብ መደረጉን ተናግረዋል።

የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ በተደረገው ጥረት በበልግ ወቅት የታየውን መልካም ተሞክሮ በመኸር ወቅትም ለመድገም፤ ጉድለቶችን ፈጥኖ በማረም የተሻለ ውጤት ለማምጣት በትኩረት ሊሰራ እንደሚገባ አሳስበዋል።

በዞኑ በትምህርት ዘርፍ የሚታዩ ችግሮችን ለመፍታትና የትምህርት ቤቶችን መሠረተ ልማት ለማሻሻል ርብርብ መደረጉንና በዚህም አበረታች ውጤት መመዝገቡንም ገልጸዋል።

በተለይም የዞኑን እምቅ ሀብትና ባህላዊ እሴቶችን በሰፊው ለማስተዋወቅ እንዲረዳ የጋሞ ቴሌቪዥን አገልግሎት ፈቃድ መሠጠቱና የሙከራ ስርጭት መጀመሩ ለዞኑ ትልቅ እድል መሆኑን ተናግረዋል።

በጉባኤው በዋና አስተዳዳሪ ማእረግ የዞኑ ም/ል ዋና አስተዳዳሪ በመሆን አቶ አባይነህ አበራ  እንዲሾሙ የቀረበውን ጥያቄ ምክር ቤቱ ተቀብሎ ሹመታቸውን አጽድቋል።

በጉባኤው የጋሞ ዞን አስተዳደር የ2015 በጀት አመት አፈጻጸም ሪፖርትና የ2016 በጀት አመት እቅድ አንደዚሁም የዞኑ ረቂቅ በጀት ቀርቦ ይፀድቃል።

የዞኑ ፍርድ ቤት እቅድና አፈጻጸም እንደሚቀርብም ይጠበቃል።

ዘጋቢ፡ ማርታ ሙሉጌታ – ከአርባምንጭ ጣቢያችን