ሁለት ወዶ አይሆንም!
በኢያሱ ታዴዎስ
የቡዳፔስቱ 19ኛው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና እነሆ ከተጠናቀቀ ሳምንት አስቆጥሯል፡፡ ወደ ስፍራው ያቀናው የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ቡድን በስድስት የተለያዩ የውድድር ዓይነቶች 34 አትሌቶችን አሳትፏል፡፡
በተሳትፎውም 2 ወርቅ፣ 4 ብር እና 3 ነሃስ በጥቅሉ 9 ሜዳሊያዎችን በመሰብሰብ ከአፍሪካ 2ኛ፣ ከዓለም ደግሞ 6ኛ ደረጃ ይዞ ማጠናቀቁ ይታወሳል፡፡
ይህ ውጤት ኢትዮጵያ በመድረኩ ከዚህ በፊት ካስመዘገበችው ጋር ሲነጻጸር ዝቅ ያለ ቢሆንም ተሳታፊ አትሌቶችና የአትሌቲክስ ፌደሬሽኑ መሪዎች እንደተናገሩትም የቡዳፔስት ከተማ የአየር ንብረት ተለዋዋጭና እጅግ ሞቀታማ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ የተጠበቀው ውጤት አልመጣም፡፡
በእርግጥ አስቀድሞ ከውድድሩ በፊት ሻምፒዮናውን የሚመጥን ዝግጅት ሲደረግ እንደነበር ከፌደሬሽኑ አካላት ዘንድ ሰምተን ነበር፡፡ መቼም ስፖርት ነውና የከተማዋ የአየር ሁኔታ በመክበዱ አትሌቶቻችንን በእጅጉ ተፈታትኖ ዝግጅት በተደረገው ልክ ውጤት መምጣት አልቻለም፡፡
ይህ ደግሞ አትሌቲክስ ቡድኑን የሚያስወቅሰው አይደለም፡፡ አትሌቶቻችን በተሳተፉባቸው የውድድር ዓይነቶች ሁሉ ሲሮጡ ከአካላዊ እንቅስቃሴያቸውና ከፊታቸው ገጽታ አየሩ እንዳልተመቻቸው የሚያሳብቅ ምልክት ታይቶባቸው ነበር፡፡
በዚያ ላይ አንዳንድ አትሌቶች ከነጉዳታቸው ሮጠዋል፤ በሩጫ መሃል ህመም የገጠማቸውም ነበሩ፡፡ በዚህ ሁሉ ፈተና ጥርሳቸውን ነክሰው ሮጠው እንደምንም ሩጫቸውን ያጠናቀቁ፣ እንዲሁም ሜዳሊያ ያገኙትን ተመልክተናል፡፡
ታዲያ እነዚህ ለሀገር ክብር የቻሉትን ዋጋ የከፈሉ አትሌቶች ከማመስገን ይልቅ መዝለፍ ተገቢ ነው ብዬ አላምንም፡፡ በማህበራዊ ሚዲያዎች አትሌቶችንና ፌደሬሽኑን የሚያብጠለጥሉ አስተያየቶች ከሰሞኑ በርከት ብለው ተመልክቻለሁ፡፡ አንዳንዶች አትሌቶችን በስም እየጠሩ ሲያበሻቅጧቸውም ተስተውሏል፡፡ ለሀገር ትልቅ ውለታ የዋሉ የፌደሬሽኑን አመራሮች ያንጓጠጡም አልጠፉም፡፡
ይህን ያህል ዱላ አትሌቲክሱ ላይ ማብዛት ለእኔ በግሌ የበሉበትን ወጪት የመስበር ያህል ይሰማኛል፡፡ ኢትዮጵያ እኮ በዓለም አቀፍ ደረጃ የምትታወቀው ከየትኛውም መስክ በላይ በአትሌቲክሱ ነው፡፡
ዝናዋም ከፍ ያለው በዚሁ ስፖርት ነው፡፡ ኢትዮጵያን ያለአትሌቲክሱ ማሰብ ፈጽሞ አይታሰብም፡፡ ለዚህ ደግሞ ቀደም ሲል ሰንደቅ አላማዋ በዓለም አደባባዮች ከፍ እንዲል ያደረጉ ጀግኖች አትሌቶቻችን ውለታቸው የበዛ ነው፡፡
የቅርብ ጊዜውን እንኳን ብናነሳ የአምናው የ2022 የኦሪገኑ አትሌቲክስ ሻምፒዮና ላይ 4 ወርቅ፣ 4 ብር እና 2 ነሐስ በጥቅሉ 10 ሜዳሊያዎችን በማስገኘት ከአፍሪካ አንደኛ፣ ከዓለም ደግሞ 2ኛ ደረጃ ይዘን እንድናጠናቅቅ ያደረጉን ጀግኖች አትሌቶቻችን ናቸው፡፡
በወቅቱ አትሌቶቹን ያላመሰገነ፣ ያላወደሰ እና የደስታ ስሜቱን ያልገለጸ አንድም ኢትዮጵያዊ አልነበረም፡፡ አትሌቶችም ከኦሪገን መልስ አዲስ አበባ አቀባበል ሲደረግላቸው ሕዝቡ ያሳያቸው ፍቅር በቃላት ከሚገለጸው በላይ ነበር፡፡
ዘንድሮም ቡዳፔስት ላይ ሀገራችንን ወክለው የተሳተፉ አብዛኛዎቹ አትሌቶች በኦሪገኑ ተሳታፊ የነበሩት ናቸው፡፡ ከላይ እንደገለጽኩት ውጤት ላለመምጣቱ ዋነኛ ምክንያት የአየሩ ምቹ አለመሆን ነው፡፡
ታዲያ አምና መሬት አይንካችሁ እያልን ስናወድሳቸው የነበሩ አትሌቶችን በአንድ ዓመት ውስጥ ውጤት አላመጣችሁም በሚል ሰበብ ስብዕናቸውን የሚጎዳ ስድብ ማከናነብ በምንም መስፈርት ትክክል ሊሆን አይቻልም።
ወይስ ውጤት ሲመጣ ብቻ ነው ጀግንነታቸው ትዝ የሚለን፡፡ ምንም ቢሆን በዓለም ማህበረሰብ ዘንድ መልካም ገጽታችንን በመገንባት ውለታ የዋሉልንን ውድ አምባሳደሮቻችን ናቸው፡፡ የትኛውንም ያህል የከፋ ውጤት ቢያስመዘግቡ ልንከፋባቸው አይገባም፡፡
አሁንም ቢሆን በቡዳፔስቱ የመጣው ውጤት አለቀ፣ ደቀቀ የሚያስብል አይደለም። ስጋታችን የነገው ከሆነ ጠንክሮ በመስራት የተሻለ ውጤት ማስመዝገብ ይቻላል፡፡ የአትሌቶችን ሞራል የሚነካ ስድብ በመስደብ ነገን መልካም ውጤት መጠበቅ ደግሞ ሌላው ከድጡ ወደ ማጡ የሚወስደን የተሳሳተ አመለካከት ነው፡፡
ይህ ሲባል ግን በቡዳፔስቱ ሻምፒዮና ላይ የተፈጠሩ ለሕዝብ ገሃድ ያልወጡ ክፍተቶች የሉም ማለት አይደለም፡፡ እንደሚኖርም አምናለሁ፡፡ ይህን እንዲያስተካልክሉ እድሉን ለፌደሬሽኑ፣ በውስጡ ላሉት አካላት እና ለአትሌቶች እንተውላቸው፡፡
አለበለዚያ ግን አትሌቶቹ መልካም ውጤት እንዲያመጡ እየፈለግን፣ በጎን ደግሞ ውጤቱ ሲጠፋ እየዘለፍን አይሆንም፡፡ ሁለት ወዶ የለምና፡፡
በአንጻሩ ደማቅ አቀባበል ከማድረግ ጀምሮ የእውቅናና የሽልማት መርሃ ግብር በማዘጋጀት የሚያስወድስ ስራ ለሰሩት ለመንግስት አካላት በሙሉ አክብሮቴን ለመግለጽ እወዳለሁ፡፡ ይኸው ተጠናክሮ ይቀጥል!!
More Stories
የብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ቀን በጌዴኦ ዞን ሁሉም ትምህርት ቤቶች በተለያዩ ኩነቶች ተከበረ
የሁሉን አቀፍ የገጠር ተደራሽ መንገድ ልማት ማጠናከር የክልሉ የመልማት አቅም ከፍ ያደርጋል – የክልሉ ትራንስፖርትና መንገድ ልማት ቢሮ
የጂንካ ዩኒቨርሲቲ ከመቀሌ ዩኒቨርሲቲ ጋር በመተባበር ባስጀመረው የእንስሳት ዝርያ ማሻሻያ ፕሮግራም ላይ ያተኮረ ውይይት መካሄድ ጀመረ