በከተማዋ በሚሰሩ መሰረተ ልማቶች ተጠቃሚነታቸውን በማረጋገጥ ላይ ይገኛሉ – በወላይታ ዞን የጉኑኖ ሐሙስ ከተማ ነዋሪዎች

በከተማዋ በሚሰሩ መሰረተ ልማቶች ተጠቃሚነታቸውን በማረጋገጥ ላይ ይገኛሉ – በወላይታ ዞን የጉኑኖ ሐሙስ ከተማ ነዋሪዎች

ሀዋሳ፡ ነሐሴ 30/2015 ዓ.ም (ደሬቴድ) በከተማዋ በሚሰሩ መሰረተ ልማቶች ተጠቃሚነታቸውን በማረጋገጥ ላይ እንደሚገኙ በወላይታ ዞን የጉኑኖ ሐሙስ ከተማ ነዋሪዎች ገለጹ፡፡

የጉኑኖ ሐሙስ ከተማን ለነዋሪዎች ምቹና ማራኪ ለማድረግ የሚያስችል ሥራ በትኩረት እየተሰራ መሆኑን የጉኑኖ ሐሙስ ከተማ ካንቲባ ጽ/ቤት ገለጸ፡፡

አቶ ፈልተሴ ፍንታ እና ወ/ሮ ምስራች ባርናባስ የጉኑኖ ሐሙስ ከተማ ነዋሪዎች ሲሆኑ በየጊዜው በጉኑኖ ሐሙስ ከተማ በሚታየው ዕድገትና በሚሰራው መሰረተ ልማት የከተማዋ ህዝብ ደስተኛ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

የጉኑኖ ሐሙስ ከተማ የከተማ አስተዳደር መዋቅር ያገኘችው በቅርብ ቢሆንም በአሁኑ ሰዓት በከተማዋ የሚታየው ፈጣን እድገትና ሰፋፊ መሰረተ ልማት ዝርጋታ ከሌሎች ከተሞች ጋር ተወዳዳሪ እንድትሆን መንገድ የሚከፍት መሆኑንም ነዋሪዎች አክለዋል፡፡

በአሁኑ ሰዓት በከተማዋ ከሚሰሩ መሰረተ ልማቶች መካከል የጌጠኛ ድንጋይ ንጣፍ፣ የከተማ ውስጥ ለውስጥ አስፋልት ስራ፣ የንፁህ መጠጥ ውሃ ፕሮጀክት፣ የውሃ መውረጂያ ዲቾችና የመብራት ዝርጋታ ተጠቃሾች መሆናቸውን የከተማዋ ነዋሪ የሆኑት ወ/ሮ ውብዓለም አማኑኤል አስረድተዋል፡፡

የጉኑኖ ሐሙስ ከተማ ለወላይታ ዞን እና ለአዲሱ ደቡብ ኢትዮጰያ ክልል ርዕሰ ከተማ ለሆነችው ለወላይታ ሶዶ ከተማ ቅርብ ከመሆኗ ጋር ተያይዞ የብዙዎች የመኖሪያ ምርጫቸው እንደሆነችም ወ/ሮ ምስራች ባርናባስ ጠቅሰዋል፡፡

በአሁኑ ሰዓት በከተማዋ የሚታየው የእድገት ለውጥና እየተሰራ ያለው መሰረተ ልማት የልማት ፈላጊ ህብረተሰብና የቆራጥ አመራሮች ሥራ ውጤት መሆኑን የጉኑኖ ሐሙስ ከተማ ማዘጋጃ ሥራ አስኪያጅ አቶ ደስታ ሲንታ ተናግረዋል፡፡

በጉኑኖ ሐሙስ ከተማ የተጀመሩ መሰረተ ልማት ሥራዎች ተጠናቅቀው ለህብረተሰብ አገልግሎት እስኪሰጡ ድረስ የከተማዋ ህዝብና መንግስት ቅንጅታዊ ተግባር እንደሚፈልግም ኃላፊው ገልጸዋል፡፡

የጉኑኖ ሐሙስ ከተማን ለነዋሪዎች ምቹና ማራኪ የማድረግ ሥራ በዕቅዱ መሰረት የሚመራ ሲሆን ዕቅዱም በህዝቡ ባለቤትነት እየተመራ ውጤት እያስመዘገበ እንደሚገኝ የጉኑኖ ሐሙስ ከተማ ካንቲባ አቶ ወንድሙ ደረጄ ተናግረዋል፡፡

የጉኑኖ ሐሙስ ከተማ ለንግድ፣ ለኢንቨስትመንትና ለኑሮ ምቹ ከመሆኗ ጋር ተያይዞ በከተማዋ በኢንቨስትመንት ዘርፍ ለመሰማራት ለሚፈልጉ ግለሰቦች የጉኑኖ ሐሙስ ከተማ ካንቲባ የማያቋርጥ ድጋፍ እንደሚያደርግም አቶ ወንድሙ ደረጄ አስታውቋል፡፡

                                                                                                                ዘጋቢ፡ ሰላሙ ማሰቦ – ከዋካ ጣቢያችን