የጊምቢቹ ኮንስትራክሽንና እንዱስትሪያል ኮሌጅ በተለያዩ መስኮች ያሰለጠናቸውን 2መቶ 61 ሰልጣኞችን አስመረቀ

ሀዋሳ፡ ነሐሴ 28/2015 ዓ.ም (ደሬቴድ) በሀዲያ ዞን የጊምቢቹ ኮንስትራክሽንና እንዱስትሪያል ኮሌጅ ለመጀመሪያ ዙር ከደረጃ 1 እስከ 4 በመደበኛ መርሀ ግብር በተለያዩ መስኮች ያሰለጠናቸውን 2መቶ 61 ሰልጣኞችን አስመረቀ።

የቴክኒክና ሙያ ስልጠና ዘርፍ ለአንድ ሀገር ብልጽግና እውን መሆን ቁልፍ ሚና ያለው መሆኑ ተጠቁሟል።

የጊምቢቹ ኮንስትራክሽንና እንዱስትሪያል ኮሌጅ ዲን አቶ ታፈሰ ላምቦሬ፤ ምንም እንኳ ኮሌጁ ወደ ስራ ከገባ ቅርብ ጊዜ ቢሆንም በሰለጠነ የሰው ኃይል በመታገዝ ብቁና ተወዳዳሪ ዜጋ ለመፍጠር በተደረገው ብርቱ ጥረት ለመጀመሪያ ዙር ከደረጃ 1 እስከ 4 በመደበኛ መርሀ ግብር በተለያዩ መስኮች ያሰለጠናቸውን 2መቶ 61 ሰልጣኞችን ማስመረቁን ገልፀዋል።

የዞኑ መቀመጫ የሆነችው ሆሳዕና ከተማ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል መቀመጫ በሆነች ማግስት መሆኑ የኮሌጁን ምረቃ ልዩ ያደርገዋል ያሉት አቶ ታፈሰ ኮሌጁ ከመማር ማስተማር ባሻገር የህብረተሰቡን ችግር ፈቺ ቴክኖሎጂዎችን በማምረት የኢንተርፕራዞች መፍለቂያ እየሆነ እንደሚገኝ አመላክተዋል።

በምረቃ ስነ ስርዓቱ የተገኙት የቀድሞ የደቡብ ክልል ቴክኒክና ሙያ ስልጠና ቢሮ ምክትል ኃላፊና የዕለቱ የክብር እንግዳ አቶ ታመነ ገብሬ በበኩላቸው የቴክኒክና ሙያ ዘርፍ ሰልጣኞች ሙያና ክህሎት ይዘው የሚወጡበት ተቋም እንደመሆኑ ለአንድ ሀገር ብልጽግና እውን መሆን ጉልህ ሚና ያለው መሆኑን ጠቁመዋል።

የቴክኒክና ሙያ ዘርፍ ከዚህ ቀደም የአመለካከት ችግር የነበረበት መሆኑን ያነሱት አቶ ታመነ ዛሬ ላይ ግን ተቋሙ በመካከለኛና ዝቅተኛ ደረጃ የሰለጠነ የሰው ኃይል በማፍራት፣ በቴክኖሎጂ ሽግግርና የሰልጣኙ የትምህርት ዕድገት መሰረት በመሆን ለሀገር ግንባታ ቁልፍ ሚና ያለው ዘርፍ ነው ብለዋል።

አቶ ታመነ አክለውም ሰልጣኞች በሰለጠኑባቸው የሙያ ዘርፎች ከስራ ጠባቂነት ተላቀው ህብረተሰቡን የማገልገል ኃላፊነት እንደሚጠበቅባቸው መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።

በምረቃው ወቅት ያነጋገርናቸው ተመራቂ ሰልጣኞችም ኮሌጁ በአቅራቢያ ተከፍቶ በአካባቢያቸው ሰልጥነው የመመረቅ እድል በማግኘታቸው ደስተኞች መሆናቸውን ጠቁመው በሰለጠኑባቸው የሙያ ዘርፎች ኃላፊነታቸውን ለመወጣት ዝግጁ መሆናቸውን ገልፀዋል።

ዘጋቢ: አማኑኤል አጤቦ – ከሆሳዕና ጣቢያችን