ማጻ ሞዴል ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ግንባታ የመሠረት ድጋይ ተቀመጠ

ማጻ ሞዴል ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ግንባታ የመሠረት ድጋይ ተቀመጠ

ሀዋሳ፡ ነሐሴ 26/2015 ዓ.ም (ደሬቴድ) የኢፌዴሪ ትምህርት ሚኒስትሩ ፕሮፈሰር ብርሃኑ ነጋ እንዲሁም በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የማህበራዊ ክላስተር አስተባባሪና የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ትምህርት ቢሮ ሀላፊ ዶክተር አበባየሁ ታደሰ በአማሮ ዞን ለሚገነባው የማጻ ሞዴል ትምህርት ቤት የመሰረት ድንጋይ አስቀምጠዋል።

የትምህርት ሚኒስትሩ ኘሮፌሰር ብርሐኑ ወደ ኬሌ ከተማ ሲደርሱ በክልልና በዞኑ አመራሮች እንዲሁም በኬሌ ከተማ ነዋሪዎች የደመቀ አቀባበል ተደርጎላቸዋል።

የትምህርት ሚኒስቴር ሚኒስትሩ ኘሮፌሰር ብርሐኑ ነጋ በበኩላቸው ተባብረን ህብረተሰቡን የሚቀይር ነገር ከሰራን ከድህነት መውጣት እንችላለን ብለዋል።

ከዚህ በኋላ ትምህርት ቤቶች በካድሬ እንዳይመሩ ይደረጋል ያሉት ኘሮፌሰር ብርሐኑ ይልቁኑ በእውቀታቸውና በክህሎታቸው ተወዳድረው በሚመሩ ዜጎች ይተካል፤ ይህ የፓርቲ አቋም ሳይሆን በመንግስት ጭምር የታመነበት ነው ብለዋል።

በዚህ ዘመን አዲሱ ትውልድ ተገቢውን ትምህርት እንዲያገኙ ለማድረግ መንግስት ርብርብ እያደረገ መሆኑን ጠቁመዋል።

ከመማር ይልቅ መስረቅን የሚለማመድ የሞራል ዝቅጠት ውስጥ የወደቀ ትውልድ እንዳይፈጠር በትጋት እንሰራለን ብለዋል ኘሮፌሰሩ።

በቀጣይ 3 ዓመታት ውስጥ በሐገር አቀፍ ደረጃ 50 ሞዴል ትምህርት ቤቶችን ለመገንባት ዕቅድ መያዙን የተናገሩት የትምህርት ሚኒስትሩ ከነዚህም መካከል 13ቱ በዚህ ዓመት ይገነባሉ ነው ያሉት።

በ2016 ዓ.ም ከሚገነቡት ውስጥ አንዱ የሆነው ይህ በአማሮ ዞን ኬሌ ከተማ የሚገኘው ማጻ ሞዴል ትምህርት ቤት ሲሆን ከመስከረም አጋማሽ ጀምሮ ወደ ግንባታ እንደሚገባ ጠቁመዋል።

እንደ ኘሮፌሰር ብርሐኑ ገለጻ ግንባታው በአንድ አመት ተጠናቅቆ በ2017 ዓ.ም መማር ማስተማር ይጀመራል ነው ያሉት።

አሁን የሚገነባው ሞደል ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት እንደ ሀገር የሚታየው የትምህርት ጥራት ችግር የሚቀርፍ መሆኑን ዶክተር አበባየሁ ታደሰ በመርሐ ግብሩ ላይ ተናግረዋል።

ዘጋቢ: አብደላ በድሩ