“አርሰናል ጨዋታዎችን ለማሸነፍ ተጨማሪ ዕድል እና የተሻለ አጨራረስ ያስፈልገዋል” ሚኬል አርቴታ
አርሰናል ከቅርብ ሳምንታት ወዲህ ጨዋታዎችን በበላይነት ቢመራም፣ ተጋጣሚዎችን ሙሉ በሙሉ አሸንፎ ለመውጣትና ጨዋታዎችን ለመጨረስ እየተቸገረ ይገኛል።
የሰሜን ለንደኑ ክለብ በሁሉም ውድድሮች ባደረጋቸው የመጨረሻ ዘጠኝ ጨዋታዎች ከአንድ በላይ በሆነ የግብ ልዩነት ያሸነፈው አንድ ጊዜ ብቻ ነው።
ትናንት ምሽት ከቦሩሲያ ዶርትሙንድ ጋር ተጫውቶ ያስመዘገበው የ1ለ1 የአቻ ውጤት የዚህ ችግር የቅርብ ጊዜ ማሳያ ሆኗል።
አርሰናል በዕረፍት ሰዓት መሪ ሆኖ ቢወጣም ነጥቦችን ጥሏል፤ ይሁን እንጂ በአሁኑ የሻምፒዮንስ ሊግ የሊግ ፌዝ ጨዋታዎች ያልተሸነፈ ሲሆን፣ በዚህ ደረጃ ሽንፈትን ካስተናገደ ከሁለት ዓመታት በላይ ሆኖታል።
መድፈኞቹ በጨዋታዎች ላይ ሰፊ የበላይነት ቢኖራቸውም፣ በተወሰኑ ደቂቃዎች ግን አቋማቸው በመቀዛቀዙ ተጋጣሚዎች ወደ ጨዋታ እንዲመለሱ እድል ይሰጣሉ።
ለአብነትም ከስላቪያ ፕራግ ጋር ከሜዳ ውጪ ባደረጉት ሻምፒዮንስ ሊግ ጨዋታ በመጀመሪያው አጋማሽ ሁለት ግቦችን ካስቆጠሩ በኋላ የአጨዋወት ጥራታቸው ወርዶ ነበር።
ባሳለፍነው ቅዳሜ ከኒውካስል ጋር በፕሪሚየር ሊጉ ተገናኝተው በዕረፍት ሰዓት መሪ ሆነው በሁለተኛው አጋማሽ 2-1 ቢመሩም፣ በኋላ ላይ ተመልሰው 2-2 ለመለያየት ተገድደዋል።
ከቡንደስሊጋው መሪ ዶርትሙንድ ጋር በተደረገው ጨዋታ አርሰናል 30 ሙከራዎችን ቢያደርግም፣ ኢላማቸውን የጠበቁት አራቱ ብቻ ነበሩ።
አሰልጣኝ ሚኬል አርቴታ ከጨዋታው በኋላ እድሎችን አለመጠቀም ቢያሳስባቸውም፣ የቡድናቸውን የሜዳ ላይ እንቅስቃሴ አድንቀዋል።
አርቴታ ሲናገሩ“የተጫወትንበት መንገድ፣ የተጋጠምነውን ቡድን ግምት ውስጥ ስናስገባ እና በሜዳ ላይ ያሳየነው ነገር እጅግ የሚያስደስት ነው፤ ከቡድኑ በጣም ትንሽ ነገር ነው የቀረው። ነገር ግን ይህን ያህል ሙከራዎች እና በርካታ እድሎችን ሲፈጠር ራሳችንን የበለጠ ማድነቅ እንዳለብን ይሰማናል“ ብለዋል።
አሰልጣኙ አክለውም “የዕድል ነገር አለ፤ የሚፈጠሩ ዕድሎችን በተሻለ መጨረስም አለብን። የቡድኑ አካሄድ ትክክለኛ ስለሆነ አጥብቀን መቀጠል አለብን“ ሲሉ ተናግረዋል።
የሚያመልጡ እድሎች ከአዕምሮ ዝግጁነት፣ ከዕድል ማጣት ወይም ከመረጋጋት ማነስ ጋር የተያያዙ ስለመሆናቸው ተጠይቀው ሲመልሱም“የአዕምሮ ጉዳይ መሆኑን አላውቅም። አንዳንድ ኳሶች እንዴት ግብ እንዳልሆኑ ስናስብ የዕድል ነገር አለ። አጨራረሱ ሊሻሻል ይችላል፣ ግን ሜዳ ላይ የነበረን እንቅስቃሴ፣ በጣም ጥሩ ነበር“ ሲሉ ተደምጠዋል።
አርቴታ የአጥቂውን ቪክቶር ግዮከሬሽ እንቅስቃሴ በተለየ ሁኔታ አድንቀዋል።
ቀደም ሲል ትችት ይቀርብበት የነበረው ከቡድን ጓደኞቹ ጋር የመገናኘት እና ጨዋታውን የማቀጣጠል ብቃቱ በዚህ ጨዋታ በጣም እንደተሻሻለ ጠቅሰዋል።
«በጣም የወደድኩት ከቡድኑ ጋር ምን ያህል እንደተሳሰረ ነው” ያሉት አርቴታ “በተለያዩ መንገዶች ብዙ ጊዜ ተጠቅመንበታል። ኳስ ማቀጣጠሉ፣ ኳስ የመያዝ ብቃቱ፣ ወደ ጀርባ የሚሰጡ ኳሶችን ማስተናገዱ እና ሜዳውን ማስፋቱ በጣም የሚደነቅ ነበር፤ ይህ ነው እኛ የፈለግነው ቪክቶር» በማለት አሰልጣኝ ሚኬል አርቴታ ገልፀዋል።
ዘጋቢ፡ሙሉቀን ባሳ
“አርሰናል ጨዋታዎችን ለማሸነፍ ተጨማሪ ዕድል እና የተሻለ አጨራረስ ያስፈልገዋል” ሚኬል አርቴታ

More Stories
በማንቸስተር ዩናይትድ እና ስፖርቲንግ ሊዝበን ማልያ የተጫወቱ 7 ተጫዋቾች
በማንቸስተር ዩናይትድ እና ስፖርቲንግ ሊዝበን ማልያ የተጫወቱ 7 ተጫዋቾች
“ቤሊንግሃም የዓለማችን ምርጡ አማካይ ተጫዋች ነው”ጆዜ ሞሪንሆ