የ2027 የአፍሪካ ዋንጫ የሚካሄድባቸው ስድስት የምሥራቅ አፍሪካ ከተሞች ይፋ ሆኑ
ከሰኔ 12 እስከ ሐምሌ 10 ቀን 2019 ዓ.ም በኬንያ፣ ታንዛኒያ እና ዩጋንዳ ጥምረት የሚዘጋጀው የ2027 የአፍሪካ ዋንጫ ውድድር የሚካሄድባቸው ስድስት አስተናጋጅ ከተሞች በአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌዴሬሽን (CAF) ይፋ ተደርገዋል።
በኮንፌዴሬሽኑ ውሳኔ መሠረት ውድድሩ የሚስተናገድባቸው ከተሞች በኬንያ ናይሮቢ፣ በታንዛኒያ ዳሬሰላም፣ አሩሻ እና ዛንዚባር እንዲሁም በዩጋንዳ ካምፓላ እና ሆይማ ናቸው።
ታንዛኒያ ሦስት ከተሞችን በማስመረጥ ሰፊውን የውድድር ድርሻ ስትይዝ፣ ዩጋንዳ በሁለት ከተሞች ጨዋታዎቹን ታስተናግዳለች።
ኬንያ በበኩሏ ሙሉ የውድድር ዝግጅቷን በዋና ከተማዋ ናይሮቢ ብቻ እንድታስተናግድ ተወስኗል።
ኬንያ በናይሮቢ ለምታስተናግዳቸው ጨዋታዎች በታላንታ ስፖርት ከተማ የሚገኘው የራይላ ኦዲንጋ ዓለም አቀፍ ስታዲየም እና የሞይ ዓለም አቀፍ ስፖርት ማዕከል (ካሳራኒ) ዋነኛ መድረኮች ይሆናሉ።
በንጎንግ ጎዳና በታሪካዊው የጃምሁሪ ሜዳ ላይ የተገነባውና 60 ሺህ ተመልካቾችን የመያዝ አቅም ያለው ዘመናዊው የራይላ ኦዲንጋ ዓለም አቀፍ ስታዲየም ግንባታው ተጠናቅቆ ለውድድሩ ዝግጁ መሆኑን የኬንያ የሀገር ውስጥ ደኅንነት እና ብሔራዊ አስተዳደር ዋና ጸሐፊ ሬይመንድ ኦሞሎ አረጋግጠዋል።
ስታዲየሙ ታኅሣሥ 27 ቀን 2019 ዓ.ም በይፋ የሚመረቅ ሲሆን፣ የምረቃ ሥነ-ሥርዓቱን ለማድመቅም የጀርመኑ ኃያል ክለብ ባየርን ሙኒክ እና የሆላንዱ አያክስ አምስተርዳም ደማቅ የወዳጅነት ጨዋታ በስታዲየሙ እንደሚያደርጉ ተገልጿል።
የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌዴሬሽን (CAF) ልዑካን ቡድንም የሦስቱን ሀገራት አጠቃላይ ዝግጁነት ለመገምገም በስታዲየሞች፣ በልምምድ ሜዳዎች፣ በትራንስፖርት መሠረተ ልማቶች እና በሆቴሎች ላይ ጥብቅ የመስክ ቁጥጥር እና ግምገማ በማካሄድ ላይ ይገኛል።
ዘጋቢ ፡ ሙሉቀን ባሳ
የ2027 የአፍሪካ ዋንጫ የሚካሄድባቸው ስድስት የምሥራቅ አፍሪካ ከተሞች ይፋ ሆኑ

More Stories
የ2025 አፍሪካ ዋንጫ ውዝግብ በሴኔጋል አሸናፊነት ተቋጨ
ሉክ ሾው ከጉዳቱ አገግሞ ወደ ልምምድ ተመለሰ
ዲያጎ ሲሞኔ የስፔን ላሊጋ የምንግዜም የአሸናፊነት ክብረወሰንን በመስበር ታሪክ ሰራ!