ዲያጎ ሲሞኔ የስፔን ላሊጋ የምንግዜም የአሸናፊነት ክብረወሰንን በመስበር ታሪክ ሰራ!
የአትሌቲኮ ማድሪዱ አሰልጣኝ ዲያጎ ሲሞኔ፤ ትናንት ምሽት ክለቡ ጌታፌን 3-0 በሆነ ሰፊ ውጤት ማሸነፉን ተከትሎ በስፔን ላሊጋ ታሪክ ብዙ ጨዋታዎችን ያሸነፈ የምንግዜም ምርጥ አሰልጣኝ በመሆን አዲስ ታሪክ አስመዝግቧል።
ሲሞኔ ጌታፌን በማሸነፍ ያገኘው ድል በላሊጋው 345ኛ ድሉ ሆኖ ተመዝግቧል።
በዚህም ቀደም ሲል በ344 ድሎች ክብረወሰኑን ይዘው የነበሩትን የቀድሞ የአትሌቲኮ ማድሪድ አሰልጣኝና የክለቡን ታላቅ ባለውለታ ሉዊስ አራጎኔስን በመብለጥ በአንደኝነት ተቀምጧል።
የ56 ዓመቱ ሲሞኔ ይህንን ታሪካዊ ድል ለመጎናጸፍ የፈጀበት 567 ጨዋታዎችን ብቻ ሲሆን፤ ይህም ሉዊስ አራጎኔስ 344 ድሎችን ለማግኘት ከፈጀባቸው 756 ጨዋታዎች በ189 ያነሰ ነው።
በተጨማሪም ሲሞኔ ሁሉንም 345 ድሎች ያስመዘገበው በአንድ ክለብ (በአትሌቲኮ ማድሪድ) ብቻ መሆኑ ስኬቱን ልዩ ያደርገዋል።
በምሽቱ ጨዋታ አትሌቲኮ ማድሪድ በአሌክስ ባኤና እና ጆኒ ካርዶሶ የመጀመሪያ አጋማሽ ግቦች እንዲሁም አሌክስ ግሪማልዶ በፍጹም ቅጣት ምት ባስቆጠራት ጎል ታግዞ ጌታፌን 3-0 በማሸነፍ ወሳኝ ሶስት ነጥቦችን አሳክቷል።
ሲሞኔ ከጨዋታው በኋላ በሰጠው አስተያየት“ይህ ስኬት በጣም ያስደስተኛል፤ ከዚህ ጀርባ እጅግ ከፍተኛ የሆነ የስራ ጥረት አለ“ ሲል ደስታውን ገልጿል።
አርጄንቲናዊው አሰልጣኝ አክሎም ቡድኑን ዘወትር ‘የሚከላከል ቡድን ነው’ እያሉ ለሚተቹ አካላት “በመከላከል ብቻ 345 የላሊጋ ጨዋታዎችን ማሸነፍ ይቻላል ወይ?” በማለት ምላሽ ሰጥቷል።
በፈረንጆቹ ታህሳስ 2011 አትሌቲኮ ማድሪድን የተረከበው ዲያጎ “ኤል ቾሎ” ሲሞኔ፣ ባለፉት 15 ዓመታት ክለቡን ከባርሴሎና እና ሪያል ማድሪድ ጋር እኩል የሚፎካከር ኃያል ቡድን አድርጎ ገንብቶታል።
በቆይታውም ሁለት የላሊጋ ዋንጫዎችን፣ ሁለት የዩሮፓ ሊግ ዋንጫዎችን እና አንድ የኮፓ ዴል ሬይ ዋንጫን ጨምሮ ስምንት ታላላቅ ክብሮችን ለክለቡ በማስገኘት የላሊጋው ህያው ፈርጥ መሆኑን በድጋሚ አረጋግጧል።
ዘጋቢ፡ ሙሉቀን ባሳ
ዲያጎ ሲሞኔ የስፔን ላሊጋ የምንግዜም የአሸናፊነት ክብረወሰንን በመስበር ታሪክ ሰራ!

More Stories
ስፖርታዊ ውድድሮች ባህላዊ እሴቶችን ለማጠናከር ያግዛሉ – የአሪ ዞን ባህልና ስፖርት ፅህፈት ቤት
ከአውሮፓ ታላላቅ ሊጎች ደካማ የሆነ የተከላካይ ክፍል ያለው ማንቸስተር ዩናይትድ
ከ15 ዓመታት በኋላ ማንቸስተር ሲቲን ነጥብ ያስጣለው ፉልሃም