አሃድ ቢዝነስ ግሩፕ በከተማው የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪ ማምረቻ ተቋም እንዲያቋቁም አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግ የወልቂጤ ከተማ አስተዳደር አስታወቀ

አሃድ ቢዝነስ ግሩፕ በከተማው የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪ ማምረቻ ተቋም እንዲያቋቁም አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግ የወልቂጤ ከተማ አስተዳደር አስታወቀ

በድርጅቱ የወልቂጤ ከተማ ወኪል አከፋፋይ የምርት መሸጫና ማሳያ ማዕከል ተመርቆ አገልግሎት መስጠት ጀምሯል።

የወልቂጤ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አቶ ሙራድ ከድር እንደገለፁት፤ መንግሥት ትኩረት ከሰጣቸው ዘርፎች አንዱ አረንጓዴ ሌጋሲን በማረጋገጥ የአየር ንብረት ለውጥን መቀነስ ነው።

በተለይም ሀገሪቱ ለነዳጅ ድጎማ ከፍተኛ በጀት እንደምታወጣ ያነሱት ከንቲባው፣ የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች ማምረትና መጠቀም የውጭ ምንዛሪ ወጪን ለመቀነስ ከሚያግዙ ዋና መፍትሔዎች አንዱ መሆኑን ገልጸዋል።

አክለውም ለድርጅቱ አስፈላጊውን ሁሉ ድጋፍ እንደሚያደርጉ በመግለፅ በክልልና በሀገር ደረጃ ተወዳዳሪ እንዲሆን ጠንክሮ መሥራት አለበት ሲሉ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።

የአሀድ ቢዝነስ ግሩፕ ምክትል ሥራ አስኪያጅ አቶ ዘሪሁን በአካሉ፤ ድርጅቱ ከአምስት በላይ ኩባንያዎችን በስሩ ያቀፈው አሃድ ቢዝነስ ግሩፕ፣ በውጭ ንግድ፣ በገቢ ንግድና በማምረቻ ዘርፎች በመሳተፍ ለሀገሪቱ የውጭ ምንዛሬ ምንጭ ከመሆን ባለፈ ከ600 በላይ ዜጎችን የሥራ ዕድል ማስገኘቱን አመልክተዋል።

በተለይ በትራንስፖርት ዘርፍ የነዳጅ ኃይልን በኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች የመተካት ራዕይን በመደገፍ፣ ጥሬ ዕቃዎችን ከውጭ በማስመጣት በራሱ ፋብሪካ የባለሁለትና የባለሦስት እግር ኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎችን እየገጣጠመ ለገበያ እያቀረበ እንደሚገኝ አቶ ዘሪሁን አመላክተዋል።

ከዚህም ባሻገር ለግል አገልግሎት፣ ለቢዝነስ፣ ለሕዝብ ትራንስፖርትና ለዕቃ ማጓጓዣ የሚያገለግሉ የተለያዩ ዘመናዊ የኤሌክትሪክ መኪናዎችን እያቀረበ መሆኑን ገልፀው ለደንበኞቹ የተሻለ አገልግሎትና የመለዋወጫ አቅርቦት ለመስጠት በቅርቡ በወልቂጤ ከተማ የመለዋወጫ ማዕከል እንደሚከፍት ተናግረዋል።

የአፍሪና ኒው ፓወር መስራችና ዋና ሥራ አስፈፃሚ ሚስተር ክሌይ እንደገለጹት፣ አፍሪና በአፍሪካ ከአስር በላይ ሀገራት የሚንቀሳቀስ ሲሆን፣ በኢትዮጵያም ከአሃድ ቢዝነስ ግሩፕ ጋር በትብብር እየሠራ ይገኛል።

ከኢትዮጵያ መልክአ ምድርና የመንገድ ሁኔታ ጋር የሚስማሙ ተሽከርካሪዎችን በተለያዩ ማሻሻያዎች እያሳደገ ወደ ገበያ እያቀረበ መሆኑንም አመልክተዋል።

የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች የትራንስፖርት ወጪን ከመቀነስ ባለፈ፣ የአገልግሎት ቅልጥፍናን ለማሳደግና የአካባቢ ብክለትን ለመቀነስም አስተዋጽኦ እንዳላቸው የመድረኩ ተሳታፊዎች አመልክተዋል።

ዘጋቢ፡ አስፍር ሙህዲን – ከወልቂጤ ጣቢያችን