ስፖርታዊ ውድድሮች ባህላዊ እሴቶችን ለማጠናከር ያግዛሉ – የአሪ ዞን ባህልና ስፖርት ፅህፈት ቤት

ስፖርታዊ ውድድሮች ባህላዊ እሴቶችን ለማጠናከር ያግዛሉ – የአሪ ዞን ባህልና ስፖርት ፅህፈት ቤት

ስፖርታዊ ውድድሮች ባህላዊ እሴቶችን ለማጠናከር እንደሚያግዝ የአሪ ዞን ባህልና ስፖርት ፅህፈት ቤት አስታወቀ።

ለ11ኛ ጊዜ የሚከበረውን የአሪ ብሔረሰብ የዘመን መለወጫ በዓልን ምክንያት በማድረግ በ10 የእግር ኳስ ቡድኖች መካከል ሲካሄድ የነበረው የድሽታ ግና ካፕ ፍፃሜውን አግኝቷል።

‎

የድሽታ ግና ካፕ አዘጋጅ ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ ይግረም ላቀው እንዳሉት፤ በድሽታ ግና ካፕ ማህበረሰቡ በስፖርቱ እየተዝናና የበዓሉን እሴቶች እንዲያዳብር የተዘጋጀ ውድድር መሆኑን ገልፀዋል።

‎

‎የአሪ ዞን ባህልና ስፖርት ፅህፈት ቤት ኃላፊ አቶ መምህሩ ጌታቸው በበኩላቸው፤ የአሪ ብሔረሰብ የዘመን መለወጫ ድሽታ ግና በዓል በዩኒስኮ እንዲመዘገብ የአብሮነትና የአንድነት እሴቱን በስፖርት ማሳደግ እንደሚያስፈልግ አስታውቀዋል።

‎

‎የ2019 ዓ.ም የድሽታ ግና በዓል በድምቀት ለማክበር በሁሉም ዘርፎች በልዩ ትኩረት እየተሰራ ይገኛል ያሉት ኃላፊው፤ የባህል ዘርፉን ይበልጥ ለማስተዋወቅ ስፖርታዊ ውድድሮች መዘጋጀታቸውን ገልፀዋል።

‎

‎የውድድሩ ተሳታፊዎችም ስፖርታዊ ጨዋነት በመላበስ ተጀምሮ እስከሚጠናቀቅ ድረስ የሚጠበቅባቸውን ኃላፊነት ስለተወጡ ኃላፊው አመስግነዋል።

በፍፃሜ ጨዋታ ፍቅር ያሸንፋል ክለብ 1ለ0 በሆነ ውጤት ጂንካ ቲክቶከሮችን በማሸነፍ የድሽታ ግና ካፕ ዋንጫ ሲረከብ፤ የጂንካ ዩኒቨርሲቲ ቡድን የውድድሩ ስፖርታዊ ጨዋነት የዋንጫ ተሸላሚ ሆኗል።

ለአሸናፊው ክለብ የዋንጫና የምስክር ወረቀት ሽልማት ተበርክቶ መርሃ ግብሩ ተጠናቋል።

ዘጋቢ፡ ተመስገን አሰፋ – ከጂንካ ጣቢያችን