የሆሳዕና ጤና ሳይንስ ኮሌጅ ከኢትዮ-ቴሌኮም ጋር በመተባበር የትምህርት አስተዳደር ሥርዓትን በይፋ አስጀመረ
የዲጂታል ሥርዓቱ ተግባራዊ መሆን የኮሌጁን የመማር ማስተማር ሂደት፣ የተማሪዎች አስተዳደር፣ የፋይናንስ አሠራርና አጠቃላይ የተቋሙን አገልግሎት በዘመናዊ ቴክኖሎጂ ለማስተዳደር የሚያስችል መሆኑ ተገልጿል።
የኮሌጁ ዲን አቶ ኤልያስ ቲራጎ በዚህ ወቅት እንደገለጹት፣ ተቋሙ በተለያዩ የሙያ ዘርፎች ብቁ ባለሙያዎችን ከማፍራት ባለፈ፣ የመማር ማስተማር ሥራውንና አጠቃላይ የሥራ እንቅስቃሴውን በቴክኖሎጂ በማስደገፍ አሠራሩን ለማቀላጠፍ እየሠራ ይገኛል።
ኢትዮጵያ በ2030 የዲጂታል ኢትዮጵያ ራዕይን እውን ለማድረግ ከያዘችው ሀገራዊ ግብ አንጻር፣ ኮሌጁም የዲጂታል ሽግግሩን ለማሳካት በትጋት እየሠራ መሆኑን አቶ ኤልያስ ገልጸዋል።
በዚህም ከኢትዮ ቴሌኮም ጋር በመተባበር የተቋሙን አሠራር ወደ ዲጂታል ሥርዓት የመቀየር ሥራ መከናወኑን አስረድተዋል።
የኮሌጁ ምክትል ዲንና የመማር ማስተማር ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ድንቁ ዳንኤል በበኩላቸው፤ ሥርዓቱ የመማር ማስተማር ሥራን ከማቀላጠፍ ባለፈ ዲጂታል ቤተ መጻሕፍትን እንዲሁም ከተማሪዎች ምዝገባ ጀምሮ እስከ ትምህርት ሂደታቸው ማጠናቀቂያ ድረስ ያሉ መረጃዎችን በአንድ ሥርዓት ለማስተዳደር እንደሚያስችል ገልጸዋል።
ይህም የፋይናንስ ሥርዓቱን ለመቆጣጠር፣ የተቋሙን የሥራ ክንውን ለማሻሻልና የመረጃ አያያዝን ይበልጥ ቀልጣፋ ለማድረግ ከፍተኛ ጥቅም እንዳለው አቶ ድንቁ አስረድተዋል።
ምክትል ዳይሬክተሩ አያይዘውም፤ የመረጃ ደህንነትን በመጠበቅ የተቋሙን አሠራር በሳይንስና በቴክኖሎጂ ለማዘመን የታቀደው ሥራ እየተጠናከረ መሆኑንም ጠቁመዋል።
በኢትዮ-ቴሌኮም የትምህርት አስተዳደር ሥርዓት ኤክስፐርት አቶ ሞሲሳ ጊቱ፣ የድረ ገጹ የትምህርት አስተዳደር ሥርዓትን በማዘመንና በማሻሻል ረገድ ጉልህ አስተዋጽኦ እንዳለው ገልጸዋል።
ሥርዓቱ ተቋማት የሥራ እንቅስቃሴያቸውን በተሻለ ሁኔታ እንዲቆጣጠሩ፣ ጊዜያቸውንና ሀብታቸውን በአግባቡ እንዲጠቀሙ እንዲሁም መረጃዎችን በአንድ ሥርዓት እንዲያስተዳድሩ እንደሚያግዝ አቶ ሞሲሳ አብራርተዋል።
ከሰው እጅ ንክኪ ጋር ተያይዘው ሊፈጠሩ የሚችሉ ስህተቶችን በመቀነስም የሥራ ቅልጥፍናን እንደሚያሳድግ ጠቁመዋል።
አገልግሎቱ በተለያዩ ተቋማት እየተስፋፋ መሆኑን የገለጹት አቶ ሞሲሳ፤ ይህም የዲጂታል ኢትዮጵያ ራዕይን እውን ለማድረግ የሚደረገውን ሀገራዊ ጥረት የሚያግዝ መሆኑን አስረድተዋል።
በተቋሙ ያነጋገርናቸው መምህራንና ተማሪዎችም፤ ዘመናዊ የዲጂታል ቴክኖሎጂዎች የትምህርት ጥራትን ለማሻሻልና የተቋሙን አገልግሎቶች በቀላልና ቀልጣፋ መንገድ ለማቅረብ ከፍተኛ ጠቀሜታ እንዳላቸው ገልጸዋል።
የትምህርት አስተዳደር ሥርዓቱ ተግባራዊ መሆን የኮሌጁን አሠራር ለማዘመን፣ የትምህርት ጥራትን ለማሳደግና ለተማሪዎች፣ ለመምህራንና ለአስተዳደሩ የተቀላጠፈ አገልግሎት ለመስጠት የሚያግዝ መሆኑ ተመልክቷል።
ዘጋቢ፡ ሄኖስ ካሳ – ከሆሳዕና ጣቢያችን

More Stories
የፖለቲካ ፓርቲዎች ተቀራርቦ በመሥራት ለሀገሪቱ ሁለንተናዊ ዕድገት የበኩላቸውን እንዲወጡ የጌዴኦ ዞን የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት አሳሰበ
ከተሞችን ፅዱና ለነዋሪዎች ምቹ ለማድረግ የጋራ ርብርብ እንደሚያስፈልግ ተገለፀ
በበጋ መስኖ 3 ነጥብ 6 ሚሊዮን ኩንታል ምርት ለመሰብሰብ ታቅዷል – የማረቆ ልዩ ወረዳ ግብርና ፅህፈት ቤት