በበጋ መስኖ 3 ነጥብ 6 ሚሊዮን ኩንታል ምርት ለመሰብሰብ ታቅዷል – የማረቆ ልዩ ወረዳ ግብርና ፅህፈት ቤት

በበጋ መስኖ 3 ነጥብ 6 ሚሊዮን ኩንታል ምርት ለመሰብሰብ ታቅዷል – የማረቆ ልዩ ወረዳ ግብርና ፅህፈት ቤት

በሁለት ዙር በሚለማ የበጋ መስኖ ልማት በተለያዩ አትክልቶች 3 ነጥብ 6 ኩንታል ምርት ለመሰብሰብ መታቀዱን የማረቆ ልዩ ወረዳ ግብርና ፅህፈት ቤት አስታውቋል።

በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የማረቆ ልዩ ወረዳ ግብርና ፅህፈት ቤት ምክትልና የእርሻ ዘርፍ ኃላፊ አቶ ማስረሻ አሰፋ እንዳሉት፤ በልዩ ወረዳው የውሃ አማራጮችን በመጠቀም በሁለት ዙር 12 ሺህ ሄክታር መሬትን በተለያዩ አትክልቶች ለማልማት ታቅዷል።

እስከ አሁን ባለው ሂደት 2 ሺ 572 ሄክታር የለማ ሲሆን ከዚህ ውስጥ 1 ሺህ 500 ሄክታር መሬት ላይ የለማ የተለያዩ አትክልቶች ምርት ለገበያ እየቀረበ እንደሆነም ገልፀዋል።

ዝኩኒና የመሳሰሉ አዳዲስ ምርቶች እየተስፋፉ መሆናቸውን የገልፁት ምክትል ኃላፊው፤ ለመስኖ ልማቱ እስከ 50 ሄክታር መሬት የማልማት አቅም ያላቸው ሶላር ፓምፖችና የውሃ መሳቢያ ሞተር ጥቅም ላይ እየዋሉ ይገኛልም ብለዋል።

አርሶ አደሩ በአካባቢው ምቹ የሆነውን የጥልቅ ጉድጓድ ውሃ በስፋት እንዲጠቀም እየተደረገ እንደሆነም ነው አቶ ማስረሻ የተናገሩት።

በልዩ ወረዳው በኢልኒኖ ክስተት ምክንያት በአዝእርት ሰብሎች ላይ የደረሰውን አሉታዊ ተፅዕኖ ለማካካስ በበጋ መስኖ ከአትክልት በተጨማሪ 200 ሄክታር መሬት ላይ በቆሎ ለማልማት ታቅዶ ወደ ተግባር መገባቱን አብራርተዋል።

በልዩ ወረዳው የደረሱ ሰብሎችን በመሰብሰብ ወቅቱን ካልጠበቀ ዝናብና ከምርት ብክነት መታደግ ተችሏል ብለዋል።

አሁን ላይ በሙሉ አቅም ወደ በጋ መስኖ መገባቱን የገለጹት ምክትል ኃላፊው፤ በልዩ ወረዳው የውሃ አማራጭ ባለባቸው አካባቢዎች በሁለት ዙር 12 ሺህ ሄክታር መሬትን በተለያዩ አትክልቶች በማልማት 3 ነጥብ 6 ሚሊዮን ኩንታል ምርት ለመሰብሰብ እቅድ ተይዞ እየተሰራ ይገኛል ብለዋል።

የቆሼ 02 ቀበሌ ነዋሪ የሆኑት አርሶአደር ሀይሌ ሀባብ በ11 ሄክታር ማሳ ላይ የውሃ አማራጮችን በመጠቀም የተለያዩ አትክልቶችን በማምረት ውጤታማ መሆናቸውን ተናግረዋል።

በክልሉ የተለያዩ አካባቢዎች የተሰማራው የጋዜጠኞች ቡድን የልዩ ወረዳውን የመኸርና የበልግ የምርት አሰባሰብ ሂደትና የበጋ መስኖ ስራዎችን ምልከታ አድርጓል።

ዘጋቢ፡ መለሰች ዘለቀ