የፖለቲካ ፓርቲዎች ተቀራርቦ በመሥራት ለሀገሪቱ ሁለንተናዊ ዕድገት የበኩላቸውን እንዲወጡ የጌዴኦ ዞን የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት አሳሰበ
ምክር ቤቱ “ሰላምና ትብብር ለሀገር ግንባታ” በሚል መሪ ቃል ጠቅላላ ጉባኤውን በዲላ ከተማ አካሂዷል።
ባለፉት ጊዜያት ምክር ቤቱ ካሉት ፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር በመቀናጀት ለሀገር ግንባታ እያበረከተ ያለው አስተዋፅኦ ከፍተኛ መሆኑን መድረኩን በንግግር የከፈቱት የጌዴኦ ዞን አስተዳደር ጽህፈት ቤት ኃላፊና የዋና አስተዳዳሪ ተወካይ አቶ ዳንኤል ስዩም ተናግረዋል።
የፖለቲካ ፓርቲዎች እርስበርስ ከመገፋፋት ይልቅ ተቀራርቦ በመሥራት ለሀገሪቱ ሁለንተናዊ ዕድገት የበኩላቸውን እንዲወጡ አቶ ዳንኤል አሳስበዋል።
የጌዴኦ ዞን የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ሰብሳቢ አቶ መስከረም ተዘራ በሀሳብ ልዩነት የሚከሰቱ አለመግባባቶችን በውይይት በመፍታት በ2018 ዓ.ም በርካታ ተግባራት መከናወናቸውን በመግለጽ በዘንድሮውም ዓመት ዕቅድ በሰላም እሴት ግንባታ ዙሪያ በትኩረት እንደሚሠሩም አንስተዋል።
በ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ማግስት የጋራ ምክር ቤቱ ጉባኤ ማካሄዱ ለሀገራዊ ለውጥና ብልጽግና ያለንን ቁርጠኝነት በግልጽ የሚያሳይ ነው ያሉት የጌዴኦ ዞን ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት የፖለቲካና አቅም ግንባታ ዘርፍ ኃላፊና የጋራ ምክር ቤቱ ምክትል ሰብሳቢ አቶ አስራት በየነ ናቸው።
ለሀገር እድገት የሚደረግ የጋራ ጥረትና ትግል በምርጫ ወቅት ብቻ የሚገደብ ሳይሆን፣ ቀጣይነት ባለው መልኩ ራሱን የቻለ ፋይዳና እሴት እየተጨመረበት የሚሄድ ተግባር መሆኑንም ኃላፊው ገልጸዋል።
ህብረተሰቡ የሚያነሳቸውን የልማትና የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎችን ለመመለስ የጋራ ምክር ቤቱ አፅንኦት ሰጥቶ እንደሚሠራም አቶ አስራት አንስተዋል።
የውይይቱ ተሳታፊዎችም በሰጡት አስተያየት በአፈፃፀሙ የተመዘገቡትን መልካም ውጤቶች በማጠናከር፣ በውስንነት የተስተዋሉትን በማረም፣ በሰላም እሴት ግንባታና የህብረተሰቡን የልማት ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ በትኩረት እንደሚሠሩም ተናግረዋል።
በመድረኩም የጌዴኦ ዞን አስተዳደር ጽህፈት ቤት ኃላፊና የዋና አስተዳዳሪ ተወካይ አቶ ዳንኤል ስዩም፣ የጌዴኦ ዞን ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት የፖለቲካና አቅም ግንባታ ዘርፍ ኃላፊና የጋራ ምክር ቤት ምክትል ሰብሳቢ አቶ አስራት በየነ፣ የጌዴኦ ዞን የፖለቲካ ፓርቲ የጋራ ምክር ቤት ሰብሳቢ አቶ መስከረም ተዘራ፣ የምክር ቤቱ አባላትና ጥሪ የተደረገላቸው ባለድርሻ አካላት ተገኝተዋል።
ዘጋቢ፡ ውብሸት ኃ/ማርያም – ከይርጋጨፌ ጣቢያችን
የፖለቲካ ፓርቲዎች ተቀራርቦ በመሥራት ለሀገሪቱ ሁለንተናዊ ዕድገት የበኩላቸውን እንዲወጡ የጌዴኦ ዞን የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት አሳሰበ

More Stories
የሆሳዕና ጤና ሳይንስ ኮሌጅ ከኢትዮ-ቴሌኮም ጋር በመተባበር የትምህርት አስተዳደር ሥርዓትን በይፋ አስጀመረ
ከተሞችን ፅዱና ለነዋሪዎች ምቹ ለማድረግ የጋራ ርብርብ እንደሚያስፈልግ ተገለፀ
በበጋ መስኖ 3 ነጥብ 6 ሚሊዮን ኩንታል ምርት ለመሰብሰብ ታቅዷል – የማረቆ ልዩ ወረዳ ግብርና ፅህፈት ቤት