በቀቤና ልዩ ወረዳ በሴቶች ልማት ህብረት ተደራጅተው በጋራ በመስራት የኢኮኖሚ አቅማቸውን ከማሳደግ ባለፈ በቤተሰብና በማህበረሰብ ውስጥ ያላቸውን ሚና ማጠናከር እንደቻሉ ያነጋገርናቸዉ ተጠቃሚ ሴቶች ገለጹ

በቀቤና ልዩ ወረዳ በሴቶች ልማት ህብረት ተደራጅተው በጋራ በመስራት የኢኮኖሚ አቅማቸውን ከማሳደግ ባለፈ በቤተሰብና በማህበረሰብ ውስጥ ያላቸውን ሚና ማጠናከር እንደቻሉ ያነጋገርናቸዉ ተጠቃሚ ሴቶች ገለጹ

በልዩ ወረዳዉ የሴቶችን ተጠቃሚነት ለማሳደግ ከባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት እየተሰራ እንደሚገኝ የቀቤና ልዩ ወረዳ ሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ጽ/ቤት ገልጿል

በቀቤና ልዩ ወረዳ በሴቶች ልማት ህብረት ከተደራጁ ሴቶች መካከል ወይዘሮ ቀመሪያ ሙዴ፣ ሙንተሃ ረሻድና እልፉ አስፋ ይገኙበታል።

መንግስት ባመቻቸላቸዉ የመሬት አቅርቦት በሴቶች ልማት ህብረት በመደራጀት በቁጠባ፣ በእንስሳት እርባታ፣ በግብርና እንዲሁም በሌሎች ገቢ በሚያስገኙ የስራ ዘርፎች ተሰማርተዉ እየሰሩ እንደሚገኙ ገልጸዋል።

ከ2002 ዓ.ም ጀምረዉ ባለፉት 17 አመታት ተደራጅተዉ በመስራታቸዉ ዉጤታማ መሆናቸዉን የገለጹት ሴቶቹ በዘንድሮ አመት በ5 ሄክታር መሬት ጤፍ፣ በቆሎና በርበሬ ማምረታቸዉን ገልጸዋል። የተሻለ ምርት ሊገኝ እንደሚችል በመጠቆም።

ሴቶች አይችሉም ከሚለዉ እሳቤ በመላቀቅ ከመኸርና በልግ እርሻ በተጨማሪ በአካባቢያቸዉ የሚገኘዉን ወንዝ በመጠቀም በመስኖ የማልማት እቅድ ስለመያዛቸዉም ተናግረዋል።

በልዩ ወረዳዉ ሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ጽ/ቤት በሚደረግላቸዉ ድጋፍ የቁጠባ ባህላቸዉ እያደገ መምጣቱን በመግለጽ ዘንድሮ ያመረቱትን ሳይጨምር ከ3 መቶ ሺህ ብር በላይ መቆጠብ እንደቻሉ አመላክተዋል።

የቀቤና ልዩ ወረዳ ሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ጽ/ቤት ባለሙያ አቶ አህመድ መኸዲ፤ በልዩ ወረዳዉ የሴቶች ልማት ህብረት በማጠናከር የተሻለ ዉጤት እንዲመጣ ድጋፍና ክትትል እየተደረገ መሆኑን ተናግረዋል።

የቀቤና ልዩ ወረዳ ሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ጽ/ቤት ኃላፊ ተወካይ ወይዘሮ አይሻ ስራጅ በበኩላቸዉ፤ በልዩ ወረዳዉ ሴቶች በተናጠል ከሚያከናውኑት የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ በተሻለ በጋራ በመደራጀት ያላቸውን አቅም፣ እውቀትና ሀብት በማቀናጀት እየተከናወነ በሚገኘዉ ስራ የተሻለ ዉጤት መመዝገቡን ገልጸዋል።

በልዩ ወረዳዉ ከ450 በላይ የሴቶች ልማት ህብረት መኖሩን የገለጹት ወይዘሮ አይሻ ሴቶቹን በቁጠባ፣ በንግድ፣ በሌማት ትሩፋት፣ በእንስሳት እርባታ፣ ንብ በማነብ፣ በግብርናና በሌሎች ዘርፎች በማደራጀት ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነታቸዉን ከማረጋገጥ በተጨማሪ ፖለቲካዊ ተሳትፎኣቸዉን ማሳደግ መቻሉን ተናግረዋል።

ሴቶች በራሳቸው ገቢ እንዲያገኙ፣ የቤተሰባቸውን የኑሮ ሁኔታ እንዲያሻሽሉ፣ ለልጆቻቸው ትምህርትና ጤና ወጪ እንዲያወጡ እንዲሁም በቤተሰብ ውሳኔ ሰጪነት ያላቸውን ተሳትፎ እንዲያሳድጉ ጽ/ቤቱ ከባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት እየሰራ ያለዉን ስራ አጠናክሮ እንደሚቀጥል ገልጸዋል።

ዘጋቢ፡ ሪያድ ሙህዲን – ከወልቂጤ ጣቢያችን