አርሰናል ከዴቪድ ራያ ጋር  አዲስ ኮንትራት ለመፈራረም  ተስማማ



የእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ ሻምፒዮኑ አርሰናል ስፔናዊውን ግብ ጠባቂ ዴቪድ ራያ ለረጅም ጊዜ በክለቡ የሚያቆየውን አዲስ ኮንትራት ለማስፈረም በመርህ ደረጃ ከስምምነት ላይ ደርሷል።

አሁን ላይ የ31 ዓመቱ ግብ ጠባቂ ኮንትራት እስከ 2028 የሚቆይ ቢሆንም፣ ክለቡ በዓለም ካሉ ምርጥ ግብ ጠባቂዎች አንዱ መሆኑን የሚመጥን አዲስ እና የተሻሻለ ውል ሊሰጠው ተዘጋጅቷል።

ይህ የራያ ስምምነት መድፈኞቹ ቁልፍ ተጫዋቾቻቸውን ለማቆየት የጀመሩት ዘመቻ አካል ሲሆን፤ ከሰሞኑ አማካዩ ዴክላን ራይስ እና ተከላካዩ ጁሪየን ቲምበር አዲስ ውል ለመፈራረም መስማማታቸው ይታወሳል።

ዴቪድ ራያ በ2023 ክረምት ከብሬንትፎርድ በ3 ሚሊየን ፓውንድ የውሰት ውል ወደ ኤምሬትስ ካመራ በኋላ፣ በ2024 በ27 ሚሊየን ፓውንድ ቋሚ ፈራሚ ሆኗል።

 በአሰልጣኝ ሚኬል አርቴታ ስር አሮን ራምስዴልን ተክቶ ቋሚ ተሰላፊ መሆን የቻለው ራያ፣ በክለቡ ቆይታው አስደናቂ ስኬቶችን አስመዝግቧል።

ስፔናዊው ግብ ጠባቂ በመጀመሪያ የውድድር ዘመኑ በ32 የሊግ ጨዋታዎች 16 ጊዜ መረቡን ሳያስደፍር በመውጣት የወርቅ ጓንት ሽልማትን ያሸነፈ ሲሆን፤ በ2024-25 (ከማትዝ ሴልስ ጋር በጋራ) እንዲሁም በ2025-26 የውድድር ዘመናት ሽልማቱን በተከታታይ በማንሳት የበላይነቱን አረጋግጧል።

ባለፈው የውድድር ዘመን አርሰናል በሊጉ ዝቅተኛውን 27 ግቦች ብቻ እንዲቆጠርበት በማድረግ እና 19 ጨዋታዎችን ግብ ሳያስተናግድ በመጨረስ፣ ክለቡ ከ22 ዓመታት በኋላ የመጀመሪያውን የፕሪሚየር ሊግ ዋንጫ እንዲያነሳ ወሳኝ ሚና ተጫውቷል።

ባለፈው ወር ስለወደፊት እጣ ፈንታው ተጠይቆ የነበረው ራያ፤ በስፔን ሊግ የመጫወት ፍላጎት እንዳለው ሳይሸሽግ፣ ነገር ግን “እዚህ (አርሰናል) በመሆኔ በጣም ደስተኛ ነኝ” ሲል ለክለቡ ያለውን ፍቅር እና ቁርጠኝነት ገልጾ ነበር።

የሚኬል አርቴታው ቡድን ከሀገራት ጨዋታዎች እረፍት መልስ ቅዳሜ ዕለት ወደ ሰሜን እንግሊዝ ተጉዞ ከኒውካስል ዩናይትድ ጋር ወሳኝ የሊግ ጨዋታውን ያደርጋል።

ዘጋቢ፡ ሙሉቀን ባሳ