ሁዋን ማታ ራሱን ከእግር ኳስ ዓለም አገለለ



በእግር ኳስ ሜዳ ላይ በሚያሳየው አስደናቂ ብቃት፣ ልዩ የኳስ እይታው እና ትህትናው በሚሊዮኖች ዘንድ ተወዳጅነትን ያተረፈው የቀድሞው የቼልሲ፣ የማንቸስተር ዩናይትድ እና የስፔን ብሔራዊ ቡድን አማካይ ሁዋን ማታ በ38 ዓመቱ ራሱን ከፕሮፌሽናል እግር ኳስ ተጫዋችነት ማግለሉን በይፋ አስታውቋል።

ማታ የእግር ኳስ ህይወቱን ማብቃቱን ሲያሳውቅ ባስተላለፈው መልዕክቱ“አንዳንድ ጊዜ መውደድ ማለት መልቀቅ ነው” በማለት ለዓመታት የኖረበትንና የሚወደውን ሜዳ በክብር መሰናበቱን ገልጿል።


ሁዋን ማታ በረጅምና ስኬታማ የእግር ኳስ ጉዞው ለክለቦቹ እና ለሀገሩ በድምሩ 740 ጨዋታዎችን አድርጎ አስደናቂ አሻራውን አሳርፏል።

በእነዚህ ጨዋታዎችም 158 ግቦችን ከመረብ ሲያሳርፍ፣175 ለግብ የሚሆኑ ኳሶችን አመቻችቶ በማቀበል የቡድን አጋሮቹን አንግሷል።

ማታ በቆየባቸው ታላላቅ ክለቦች እና በስፔን ብሔራዊ ቡድን ማሊያ 11 ታላላቅ ዋንጫዎችን ከፍ አድርጎ ማንሳት ችሏል።

ከእነዚህም መካከል የዓለም ዋንጫ፣ የአውሮፓ ዋንጫ ፣ የአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግ፣ ዩሮፓ ሊግ እና የእንግሊዝ ኤፍ ኤ ካፕ በዋናነት ይጠቀሳሉ።

በተለይም በቼልሲ እና በማንቸስተር ዩናይትድ ቆይታው በደጋፊዎች ዘንድ እጅግ ተወዳጅ የነበረው ማታ፣ ከሜዳ ውጭም በሚያደርጋቸው የበጎ አድራጎት ስራዎች የብዙዎች አርዓያ በመሆን ይታወቃል።

የ38 ዓመቱ ጥበበኛ ከሜዳ ቢሰናበትም፣ በእግር ኳስ ዓለም የፈጠራቸው አስደናቂ ቅጽበቶች እና ያስመዘገባቸው ታላላቅ ድሎች በስፖርቱ ታሪክ ለዘላለም ሲታወሱ ይኖራሉ።

ዘጋቢ፡ ሙሉቀን ባሳ