አርባ ምንጭን ያገነነው ሌላኛው የተፈጥሮ ውበት

አርባ ምንጭን ያገነነው ሌላኛው የተፈጥሮ ውበት

እዚህ አካባቢ ሆኖ ተፈጥሮን አለማድነቅ አይቻልም፡፡ እንዲያውም ልብ ብሎ የተመለከተው ተፈጥሮ አድልቷል ማለቱ አይቀርም፡፡ መገኛችንን በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ጋሞ ምድር ላይ የበቀለ ድንቅ ተፈጥሯዊ ስፍራ አደረግን፡፡ ስፍራው የፈጣሪን ድንቅ ሥራ እንድናደንቅ የሚያስገድድ ነው፡፡ እስቲ በምናብ አብረን እንጓዝ፡-

መዳረሻዎን “የምድር ገነት” ተብላ የምትጠራው አርባ ምንጭ ከተማ ላይ ካደረጉና በከተማዋ ብቻ ለመሰንበት ቆርጠው ከሆነ በእርግጠኝነት ሃሳብዎን መቀየርዎ አይቀርም፡፡ አርባ ምንጭ ሄደው በዙሪያዋ የሚገኙ የተፈጥሮ ፀጋዎች ሳይመለከቱ ከተመለሱ በእርግጥም ይቆጭዎታል፡፡

አርባ ምንጭ ታይተው የማይጠገቡ፣ ተጎብኝተው በቃኝ የማያስብሉ ውብ ስፍራዎችን የተቸረች እንደ ስሟ የምድር ገነት ናት፡፡ ይህን የሚገነዘበው በጉያዎቿና በዙሪያዋ የተሸሸጉ ማራኪ ስፍራዎችን የመጎብኘት ዕድል ያገኘ ሰው ነው፡፡

በታላቁ ስምጥ ሸለቆ ውስጥ የተገኘችው ከተማዋ ሞቃታማ አየር ቢኖራትም ዙሪያዋን ጠቅጠቅ ባሉ ደኖች የተከበበች ናት፡፡ የስምጥ ሸለቆ አካል የሆኑት አባያ እና ጫሞ ሐይቆች መካከልም የተቆረቆረች ናት፡፡ በሁለቱ ሐይቆች መካከል የተዘረጋው “የእግዜር ድልድይ” የሚል ተለምዷዊ ስም የተሰጠው የተፈጥሮ ገጽታም ስሟን አግንኖላታል፡፡

ከሁሉም ደግሞ የስሟ ምክንያት የሆኑት ከአርባ በላይ ቁጥር ያላቸው ኩልል ያሉ ምንጮች ለዓይን ብቻ ሳይሆን ለሰውነትም ጠገን ናቸው፡፡ በፋብሪካ ተጣርተው ከሚወጡ የታሸጉ ውሃዎች ይልቅ ጥምን ያረካሉ፡፡ ዙሪያ ገባቸው ዓይነ ግቡ በሆኑ እጽዋት የታጀቡ ናቸው፡፡

ከከተማዋ በስተምስራቅ እና በስተደቡብ አቅጣጫ ተንጣልለው የሰፈሩት አባያ እና ጫሞ ሐይቆችም ሌሎች ማራኪና ጎብኚዎችን የሚጠሩ መስህቦች ናቸው፡፡

አሁን ምናባዊ ምልከታችንን ወደ ዋናው የዛሬው መስህብ አዙረናል፡፡ ከውቢቷ አርባ ምንጭ ከተማ በስተምስራቅ እና ጥቂት ደግሞ ደቡባዊ አቅጣጫ የተወሰነ እንጓዝ፡፡ ልክ 32 ኪሎ ሜትር እንደተጓዝን በከተማዋ ዙሪያ የተንጣለለው ሌላኛው ተፈጥሯዊ ውበት ነጭ ሳር ብሔራዊ ፓርክን እናገኛለን፡፡

ነጭ ሳር ብሄራዊ ፓርክ አጠቃላይ 514 ስኬዌር ኪሎ ሜትር ስፋት አለው፡፡ በአባያ እና ጫሞ ሐይቆች መካከል ይገኛል፡፡ የሐይቁ 15 በመቶ የሚሆነው ስፍራ በውሃ የተሸፈነና ቀሪው ደግሞ የብስ እንደሆነ መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡

ነጭ ሳር የሚለው ስያሜውንም ሰፋፊ ከሆኑና ሜዳውን ከሸፈኑት ሳሮች ነው ያገኘው፡፡ ፓርኩ ሳሮችን ጨምሮ ደንን፣ የተፈጥሮ ፍል ውሃዎችንና ከ40 በላይ የሆኑትን ምንጮችንም ያካልላል፡፡

ፓርኩ በ1967 ዓ.ም ነበር በብሔራዊ ፓርክነት የተመሰረተው፡፡ በተባበሩት መንግስታት የትምህርት፣ የሳይንስና የባህል ድርጅት (ዩኔሴስኮ) ባለሙያዎች ጥናትና ምክረ ሃሳብ መነሻነት በኢትዮጵያ መንግስት በወቅቱ የዱር እንስሳት ጥበቃ ድርጅት አማካይነት መቋቋሙን ነው መረጃዎች የሚቁሙት፡፡

የፓርኩ መገለጫዎች ብዙ ናቸው፡፡ ከ1 ሺህ በላይ የእጽዋት ዝርያዎች ያሉት ሲሆን ልዩ ውበት በማጎናጸፍ ይታወቃሉ፡፡ ስነምህዳሩ ለብዝሃ ሕይወት መኖሪያነት ምቹ ነው፡፡ በዚህም ምክንያት ከእጽዋት ባሻገር አጥቢ እንስሳት እና አሳዎች በብዛት ይገኛሉ፡፡ የፓርኩ አካላት የሆኑት የውሃ አካላትም የጉማሬ እና አዞ መኖሪያ ናቸው፡፡

ከ300 በላይ የአዕዋፋት ዝርያዎችም መኖሪያቸው በዚሁ ነጭ ሳር ፓርክ ነው፡፡ ጥናቶች እንደሚያመለክቱትም ከ103 በላይ አጥቢ የዱር እንስሳት ይገኛሉ፡፡ ከአጥቢ እንስሳቱም መካከል የሜዳ አህያ፣ የሜዳ ፍየል፣ አጋዘን፣ ድኩላ፣ ድፋርሳ፣ ጉማሬ፣ ቆርኬ እና ሚዳቋ የመሳሰሉ ሳር በል እንስሳት ይገኙበታል፡፡

ስጋ በል ከሆኑት ደግሞ አንበሳ፣ ነብር፣ አቦ ሸማኔ፣ ጅብ እና ቀበሮ ይጠቀሳሉ፡፡

ብሔራዊ ፓርኩ እነዚህን ሁሉ የተፈጥሮ ሃብቶች የታደለ ነው፡፡ በግዝፈቱም ሆነ በብዝሃነቱ በሀገራችን ትልቅ የቱሪስት መዳረሻ ከሆኑት ከቀዳሚዎቹ ተርታ ይሰለፋል፡፡

ግን ደግሞ አስፈላጊው ጥበቃ ሊደረግለትም የሚገባው ነው፡፡ ፓርኩ ላይ በከብቶች ግጦሽ፣ በመጤ አረም መስፋፋት፣ በሰፈራ እና በእርሻ መስፋፋት ምክንያት ስጋት መደቀኑን በተለያዩ ጊዜያት በመገናኛ ብዙሃን ተወስቷል፡፡

ነጭ ሳር ብሔራዊ ፓርክ የሀገራችን አንጡራ ሃብት ነውና ሁሉም ሊጠብቀውና ሊንከባከበው ይገባል እንላለን፡፡ ሰላም!!

ዘጋቢ፡- ኢያሱ ታዴዎስ