ለክትባት ዘመቻው ስኬት ሚዲያዎችና ባለድርሻ አካላት ኃላፊነታቸውን በአግባቡ እንዲወጡ ጥሪ ቀረበ

በክልሉ ለሚገኙ ዕድሚያቸው ከአምስት ዓመት በታች ለሆኑ ከ 1 ነጥብ 5 ሚሊየን በላይ ሕፃናት የሚሰጠው የፖሊዮ ክትባት ዘመቻ ውጤታማ እንዲሆን ሚዲያዎችና ባለድርሻ አካላት ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ ጥሪ ቀረበ፡፡

‎የክልሉ ጤና ቢሮ እና የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት በጋራ ባዘጋጁት መድረክ ላይ፣ ‎የክትባት መድኃኒት ጥራትና ፈዋሽነትን ለማረጋገጥ ማቀዝቀዣዎችን በአግባቡ መጠቀም እንደሚገባም ተመላክቷል።

‎

‎ፖሊዮ በቫይረስ የሚተላለፍ እና ሕፃናት ላይ ከፍተኛ የጤና ጉዳት የሚያስከትል በሽታ መሆኑን የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ምክትል ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ምንተስኖት መልካ ገልጸዋል።

‎

‎ከህዳር 12 እስከ 15 ቀን 2019 ዓ.ም ድረስ በክልሉ በሚካሄደው የቤት ለቤት ዘመቻ ከዚህ ቀደም የተከተቡም ሆኑ ያልተከተቡ ከ1 ነጥብ 5 ሚሊዮን በላይ ሕፃናት የፖሊዮ ክትባቱን እንደሚወስዱ ዳይሬክተሩ አስታውቀዋል።

‎

‎የክትባት ዘመቻውን ይበልጥ ውጤታማ ለማድረግ ክልሉ አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግ የገለጹት ዳይሬክተሩ፤ መዋቅሮች መከተብ የሚገባውን ህጻን በሙሉ ተደራሽ ለማድረግ ጥረት እንዲያደርጉ አሳስበዋል።

‎

‎ከፖሊዮ ክትባት በተጨማሪም መደበኛ ክትባታቸውን ያቋረጡ ሕፃናትን ለይቶ የመከተብ፣ የእናቶችና ሕፃናት የሥርዓተ-ምግብ ልየታ የማድረግ፣ የአጣዳፊ የልጅነት ልምሻ እና የኢቦላ ወረርሽኝ ቅኝት ሥራዎች በቅንጅት እንደሚከናወኑ ዶክተር ምንተስኖት ለተሳታፊዎች አስገንዝበዋል።

‎

‎የደቡብ ኢትዮጲያ ክልል ጤና ቢሮ ኃላፊ ተወካይና የጤና ፕሮግራሞች አስተባባሪ አቶ ናፍቆት ብርሃኑ በበኩላቸው፤ ለዘመቻው ስኬት የክልሉ መዋቅሮች አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚሰጡ አመላክተዋል።

‎

‎የፓሊዮ በሽታ ክትባት ሽፋንን በአግባቡ በመፈጸም አስፈላጊ መረጃዎችን አደራጅቶ መያዝ ያሻል ያሉት አቶ ናፍቆት፤ የክትባት መድኃኒት ጥራትና ፈዋሽነት ለማረጋገጥ የቅዝቃዜ ሰንሰለትን መጠበቅ እንደሚገባም ጠቁመዋል።

‎

‎የክልሉ ጤና ቢሮ የሕዝብ ግንኙነትና ኮሚኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ ሰራዊት ዲባባ በበኩላቸው፤ የግንዛቤ ማስጨበጫ ንቅናቄውን ለማቀጣጠል የሚዲያ ተቋማት ድርሻ ከፍተኛ በመሆኑ ትክክለኛ እና ወቅታዊ መረጃዎችን ለኅብረተሰቡ በፍጥነት በማድረስ ለፓሊዮ ክትባት ዘመቻው ስኬት የበኩላቸውን እንዲወጡ ጥሪ አቅርበዋል።

‎

‎በአርባምንጭ ከተማ በተካሄደው የንቅናቄ መድረክ ላይ ‎በፓሊዮ ክትባት ዘመቻና የህዝብ ግንኙነትና ሚዲያ ሚና ዙሪያ የመወያያ ሰነድ ቀርቦ ወይይት ተደርጓል፡፡

በመድረኩ ከተለያዩ የክልሉ መዋቅሮች የተሳተፉ ባለድርሻ አካላት አስፈላጊውን ቅድመ ዝግጅት በማድረግ በፓሊዮ ክትባት ዙሪያ የማኅበረሰቡን ግንዛቤ ለማሳደግ እንደሚሰሩም ቃል‎ ገብተዋል።

‎

‎ዘጋቢ፡ አሰግድ ተረፈ – ከአርባምንጭ ጣቢያችን