ሃሪ ኬን ኪሊያን ምባፔን በ28 ነጥብ ብቻ በመበለጥ ባሎንዶሩን ማሸነፉ ይፋ ሆነ
የ2025-26 የውድድር ዘመን የዓለማችን ምርጥ እግር ኳስ ተጫዋች በመሆን የወርቃማዋን ኳስ (ባሎንዲኦር) ክብር የተቀዳጀው የእንግሊዝ ብሔራዊ ቡድን እና የባየርን ሙኒክ አጥቂ ሃሪ ኬን፣ ሽልማቱን ያሸነፈው ሁለተኛ የወጣውን ኪሊያን ምባፔን በ28 ነጥብ ብቻ በልጦ መሆኑን የአዘጋጅ ኮሚቴው ይፋ ያደረገው ዝርዝር መረጃ አመልክቷል።
ከቀናት በፊት በለንደን በተካሄደው የሽልማት ሥነ-ሥርዓት ላይ የዓመቱ ምርጥ አጥቂ ሽልማትን ጨምሮ የባሎንዶር አሸናፊ የሆነው የ33 ዓመቱ ኬን፣ ባለፈው የውድድር ዘመን ለክለቡ እና ለሀገሩ ባደረጋቸው 65 ጨዋታዎች 73 ግቦችን ማስቆጠር ችሏል።
ከ100 አገራት የተወጣጡ ስፖርት ጋዜጠኞች በሰጡት ድምፅ መሠረት ሃሪ ኬን 1 ሺህ 55 ነጥብ በማግኘት የአንደኝነት ደረጃን ይዟል።
ኪሊያን ምባፔ በበኩሉ በ1 ሺህ 27 ነጥብ በጠባብ የነጥብ ልዩነት ተከታዩን ደረጃ ይዞ አጠናቋል።
እንዲሁም ላሚን ያማል በ881 ነጥብ ሦስተኛ ደረጃን ይዟል።
ይህ በሃሪ ኬን እና ኪሊያን ምባፔ መካከል የተፈጠረው የ28 ነጥብ ልዩነት በባሎንዶር ሽልማት ታሪክ ከተመዘገቡ እጅግ ተቀራራቢና በጠባብ የነጥብ ልዩነት ከተጠናቀቁ ውጤቶች መካከል አንዱ ሆኖ ተመዝግቧል።
እ.ኤ.አ. በ2019 ሊዮኔል ሜሲ ቨርጅል ቫን ዳይክን በ7 ነጥብ ካሸነፈ ወዲህ ይህ የመጀመሪያው ተቀራራቢ ውጤት ሲሆን፣ በታሪክ እጅግ በጠበበ ልዩነት አሸናፊው የተለየው ማቲያስ ሳመር ሮናልዶ ናዛሪዮን እ.ኤ.አ በ1996 (በ1 ነጥብ) እና ቦቢ ቻርልተን ኤውሴቢዮን በ1966 (በ 1 ነጥብ) ያሸነፉባቸው አጋጣሚዎች ናቸው።
ሃሪ ኬን ባለፈው ዓመት ባየርን ሙኒክን ለቡንደስሊጋ እና ለጀርመን ዋንጫ ድል ያበቃ ሲሆን የጀርመን ሱፐር ካፕንም አሸንፏል።
በተጨማሪም የእንግሊዝ ብሔራዊ ቡድንን በአምበልነት መርቶ በዓለም ዋንጫ ሦስተኛ ደረጃን እንዲይዙ አድርጓል።
ኪሊያን ምባፔ በአንፃሩ በላሊጋ እና በቻምፒየንስ ሊግ 40 ግቦችን ከማስቆጠሩ ባሻገር፣ በዓለም ዋንጫ 10 ግቦችን በማስቆጠር ለሁለተኛ ተከታታይ ጊዜ የውድድሩን ኮከብ ግብ አስቆጣሪነት አሸንፏል።
ድምፅ አሰጣጡ የተካሄደው ከ100 ሀገራት በተወጣጡ ጋዜጠኞች ሲሆን፣ እያንዳንዱ መራጭ ለ10 ተጫዋቾች እንደየደረጃቸው ነጥብ በመስጠት በሰጡት ድምፅ ድምር ውጤት አሸናፊው ተለይቷል።
ዘጋቢ፡ ሙሉቀን ባሳ

More Stories
ቼልሲ ማንቸስተር ዩናይትድን በመርታት ወደ አሸናፊነት ተመለሰ
ማንችስተር ዩናይትድ ፈርሚን ሎፔዝን ለማስፈረም ፍላጎት ማሳየቱ ተገለጸ
ካርሎስ ቴቬዝ ከማንቼስተር ዩናይትድ ወደ ማንቼስተር ሲቲ ያደረገው ዝውውር በበቀል ላይ የተመሰረተ እንደነበር ተናገረ