ጤናማ ማህበረሰብ አምራችና የልማት መሰረት በመሆኑ በክልሉ ጠንካራ የጤና ልማት ስርዓት መገንባት እንደሚገባ የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ተስፋዬ በልጅጌ (ዶ/ር) ገለጹ
”ኑ! ለነገ የጤና ወጪያችን በጋራ እናስብ !” በሚል መሪ ቃል የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ጤና ቢሮ የ2019 በጀት ዓመት የማህበረሰብ አቀፍ ጤና መድህን (ማአጤመ) ማጠናከሪያ ንቅናቄ መድረክ በጂንካ ከተማ አካሂዷል፡፡
የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ርዕሰ መስተዳደር ተስፋዬ በልጅጌ(ዶ/ር) ጤናማ ማህበረሰብ አምራችና የልማት መሰረት በመሆኑ ህብረተሰቡ ፈጣንና ቀልጣፋ የጤና አገልግሎት በፍትሀዊነት እንዲያገኝ ጠንካራ የጤና ልማት ስርዓትን መገንባት እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡
አክለዉም የእናቶችና የህፃናት ጤና እንክብካቤ የእናቶች ሞት መቀነስ ፅዱ ኢትዮጵያን መፍጠር ላይ ለዉጦች ቢኖሩም ትኩረት እንደሚፈልግ አስታዉሰዉ በጤናዉ ዘርፍ መረጃ ከሰዉ ህይወት ጋር የሚገናኝ በመሆኑ የመረጃ አያያዝ ጥራት የአንቡላን አጠቃቀም የአገልግሎት አሰጣጥ ጥራት የባለሙያዎች ብቃት ስነምግባርና ተነሳሽነት ስራዎችን ዲጂታላይዝ በማድረግ የህብረተሰቡ የጤና አገልግሎት ተጠቃሚነት ላይ በዘርፉ የሚመለከተዉ አካል በትኩረት በመስራት በሁሉም ምርጥ የሚባል የተሻለ አፈፃፀም ማስመዝገብ ይገባልም ብለዋል፡፡
የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ጤና ቢሮ ኃላፊ አቶ ዳዊት ደሳለኝ በበኩላቸዉ እንደአሉት፤ ህብረተሰቡ ፈጣንና ቀልጣፋ የጤና አገልግሎት እንዲያገኝ ለማስቻል እየተሰራ መሆኑን አንስተዉ የጤና መድህን አገልግሎት ለዜጎች ጤና መሻሻል ዋስትና በመሆኑ አገልግሎትን በማስፋትና የሕብረተሰቡን ተሳትፎ በማጠናከር ዜጎች በትንሽ ወጪ የተሻለ የጤና አገልግሎት እንዲያገኙ ለማድረግ ሲሰራ ቆይቷል።
በጤና መድህን አገልግሎት በ2018 በጀት ዓመት ከ1 ሚልየን በላይ የህብረተሰብ ክፍሎችን ተጠቃሚ ማድረግ የተቻለ ሲሆን በ2019 በጀት ዓመትም ከዚህ የበለጠ መስራት ይጠበቃል ብለዋል፡፡
የኣሪ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ አፌዶ ወርቁ እንኳን ደህና መጣችሁ መልዕክት አስተላልፈው ለዜጎች ጤና መሻሻልና መጎልበት ማህበረሰቡ በአግባቡ የጤና መድህን አገልግሎት ተጠቃሚ እንዲሆን ለማስቻል በትኩረት እንደሚሰራ በንግግራቸው አስረድተዋል።
በመድረኩ የተለያዩ ሰነዶች ቀርበዉ ዉይይት ተደርጎባቸዉ የተለያዩ ሀሳብና አስተያየቶች ቀርበዉ ምላሽና ማብራሪያ ተሰጥቶባቸዉ በጤና መድህን አገልግሎት አሰጣጥ የተሻለ አፈፃፀም ላላቸዉ ግለሰቦችና ተቋማት የእዉቅና ሽልማት ተበርክቷል፡፡
በመርሃ ግብሩ ላይ የክልሉ ርዕሰ መስተዳደር ተስፋዬ በልጂጌ(ዶ/ር) ጨምሮ የመንግስት ዋና ተጠሪ አበባየሁ ታደሰ (ዶ/ር) እና ሎሎች የተለያዩ የክልል የስራ ኃላፊዎች የዞንና የወረዳ አስተዳዳሪዎች ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች ተገኝተዋል፡፡
ዘጋቢ፡ በናወርቅ መንግስቱ – ከጂንካ ጣቢያችን

More Stories
ጠንካራ ተቋም በመመስረት ህዝብና መንግስት ከሴክተሩ የሚጠብቁትን ውጤት ለማስመዝገብ እንሰራለን – የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ሥራና ክህሎት ቢሮ ኃላፊ
የደቡብ ኢትዮጵያ ክልላዊ መንግስት ርዕሰ መስተዳድር ተስፋዬ በልጅጌ (ዶ/ር) የትምህርት ዘርፍ ስራ በተለመደ መልክ ሳይሆን በአዲስ መልክ የሚመራ መሆን አለበት ሲሉ ገለፁ
የደቡብ ኢትዮጵያ ክልላዊ መንግስት ርዕሰ መስተዳድር ተስፋዬ በልጅጌ (ዶ/ር) በተገኙበት የክልሉ የ2019 የትምህርት ጉባኤ በጂንካ ከተማ እየተካሄደ