የሼሪዓ ፍርድ ቤቶችን አቅም በማጎልበት እና በመደገፍ የፍትህ ስርዓቱ አጋዥ ሆነው እንዲሰሩ የማድረጉ ስራ ተጠናክሮ ይቀጥላል – የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት
የሼሪዓ ፍርድ ቤቶችን አቅም በማጎልበት እና በመደገፍ የፍትህ ስርዓቱ አጋዥ ሆነው እንዲሰሩ የማድረጉ ስራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት አስታወቀ።
የሼሪዓ ፍርድ ቤት ተደራሽነት እና ተቋማዊ አቅም ማሻሻያ ጥናት ባለድርሻ አካላት በተገኙበት ተገምግሟል።
የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት አቶ ቆጭቶ ገብረማርያም በዚሁ ወቅት እንዳሉት፤ የፍትህ ተቋማቱን ከሚያግዙ የፍትህ ስርዓቶች ውስጥ የሼሪዓ ፍርድ ቤት ተጠቃሽ መሆኑን ጠቅሰው፤ በተገቢው ከመደራጀት እና ተደራሽ ከመሆን አንጻር ውስንነቶች እንዳሉባቸው አንስተዋል፡፡
በክልሉ አንድ ከፍተኛ እና ሶስት የከተማ የሼሪያ ፍርድ ቤቶች መኖራቸውን ያወሱት ፕሬዝዳንቱ፤ በሰው ሀይል እና በግብዓት አለመሟላት እዲሁም በተገቢው ለህብረተሰቡ ተደራሽ አለመሆን ችግሮች እንዳሉባቸው ገልፀዋል።
እነዚህን ችግሮች ለመፍታት እና መፍትሔ ለማስቀመጥ የአሰራር ስርዓቱን ማሻሻል የሚያግዝ በህግ ባለሙያዎች የዳሰሳ ጥናት መደረጉን ጠቁመው፤ ጥናቱ ከባለድርሻ አካላት ጋር ውይይት እንደተደረገበትና ወደስራ ለማስገባት አቅም እንደሚፈጥር አመላክተዋል፡፡
የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል ሼሪዓ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት ሼህ አህመድ አድማሱ በበኩላቸው፤ በክልሉ የሼሪያ ፍርድ ቤት አገልግሎት ማግኘት ያልቻሉ እንዳሉም ጠቅሰዋል።
ይህንን ችግር ለመቅረፍ የሼሪያ ፍርድ ቤቶችን መዋቅር ማጠናከር እንደሚያስፈልግ እና የእምነቱ ተከታዮች የቤተሰብ፣ ጋብቻ፣ የፍቺ፣ የውርስና የመሳሰሉ ጉዳዮችን ርቀት ቦታ ሳይጓዙ በአቅራቢያ የፍትህ አገልግሎት እንዲያገኙ ያስችላል ብለዋል።
የክልሉን የፍትህ ተደራሽነት ይበልጥ የሚያጠናክር፣ የህዝቡን አመኔታ የሚያሳድግ፣ ፈጣን፣ ቀልጣፋና ጥራት ያለው ፍትህ አገልግሎት ለማህበረሰቡ ለማቅረብ የሚደረገውን ጥረት የሚያፋጥን መሆኑን ተናግረዋል።
የዳሰሳ ጥናት ያደረጉት በሚዛን ቴፒ ዩኒቨርሲቲ የህግ መምህር እና የህግ ባለሙያ የሆኑት አብዱረህማን ሰይድ በበኩላቸው፤ የሼሪዓ ፍርድ ቤቱ ያሉበትን ችግሮች ከነመፍትሄው የሚያመላክት የዳሰሳ ጥናት መደረጉን ገልፀዋል፡፡
ከግብዓት አቅርቦት ችግር ባለፈ ያሉ የክህሎት ክፍተቶችን ለመሙላትና በእውቀት የታገዙ ባለሙያዎችን ወደሼሪዓ ፍርድ ቤቱ በማምጣት ለሙስሊሙ ማህበረሰብ ፈጣን፣ ቀልጣፋ እና ተደራሽ የሆነ ፍትህ መስጠት ያስችላልም ብለዋል።
የቀረበውን ጥናት ተንተርሶ በተግባር መተርጎም እንደሚገባ ገልፀው፤ በክልሉ ያሉትን ሶስት የሼሪዓ ፍርድ ቤቶችን ቁጥር ወደ አስራ ስምንት ከፍ ለማድረግ መታቀዱንም ጠቁመዋል።
የቤንች ሸኮ ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት አቶ ቢኒያም ባቡ እና የቦንጋ ከተማ አስተዳደር ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት አቶ አዴሎ ሀይሌ በበኩላቸው፤ የሼሪዓ ፍርድ ቤት የፍትህ ስርዓቱን በማገዝ በኩል የራሳቸውን ሚና እንደሚጫወቱ አውስተዋል።
ነገር ግን የግብዓት እጥረት፣ ተደራሽ አለመሆን፣ የሰው ሀይል እጥረት እና በበጀት አለመደገፍ ተግዳሮቶች መሆናቸውን ጠቅሰው፤ እነዚህ ችግሮች ተቀርፈው የተሻለ ተግባር ለመፈጸም ሰነዱ ጥሩ አቅም እንደሚፈጥር አንስተዋል።
በውይይቱ የተሳተፉ የሙስሊም ማህበረሰብ ተወካዮች በበኩላቸው፤ በሼሪዓ ፍርድ ቤቶች የሚታዩ የአሰራር ችግሮችን በዳሰሳ ጥናቱ ተለይቶ መውጣቱ ጥሩ መሆኑን አንስተው፤ የተጠናው ጥናት ወደተግባር እንዲገባ ሁሉም ባለድርሻ አካላት ሊረባረቡ እንደሚገባ እና ህዝበ ሙስሊሙ የበኩሉን ድርሻ ሊወጡ እንደሚገባ ጠቁመዋል።
ዘጋቢ፡ አብዮት በቀለ – ከሚዛን ጣቢያችን

More Stories
የአንድ ማህበረሰብ ቋንቋ ለትውልድ እንዲተላለፍ እና በጽሑፍ እንዲበለጽግ የቋንቋ ሰዋሰው ጥናት ወሳኝ ሚና አለው – የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል መንግስት ባህልና ስፖርት ቢሮ
ርዕሰ መስተዳድር ተስፋዬ በልጅጌ (ዶ/ር) ጂንካ ከተማ ገቡ
በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል መንግሥት የብሄረሰቦች ምክር ቤት 21ኛው የኢትዮጵያ ብሄሮች፣ ብሄረሰቦች እና ህዝቦች ቀን በዓልን አስመልክቶ የተዘጋጀ የውይይት መድረክ እየተካሄደ ነው