አሰልጣኝ መሳይ ተፈሪ የ10 ጨዋታዎች ቅጣት ተላለፈባቸው
የወላይታ ድቻው ዋና አሰልጣኝ መሳይ ተፈሪ የ10 ጨዋታዎች ቅጣት ተላልፎባቸዋል።
አሰልጣኙ ይህ ቅጣት የተላለፈባቸው በሲቢኢ የኢትዮጵያ ፕሪሚዬር ሊግ 3ኛ ሳምንት መርሐግብር ወላይታ ድቻ በሀላባ ስታዲየም በባህርዳር ከተማ 3ለ1 በተሸነፈበት ጨዋታ ባሳዩት ባህሪ ምክንያት መሆኑ ተገልጿል።
አሰልጣኝ መሳይ ተፈሪ በጨዋታው 90+4ኛው ደቂቃ ላይ ዳኛን አፀያፊ ስድብ በመሳደብ በቀይ ካርድ ከጨዋታ ሜዳ ስለመውጣታቸው ሪፖርት መቅረቡን የኢትዮጵያ ፕሪሚዬር ሊግ አክሲዮን ማህበር አሳውቋል።
አሰልጣኙ ለፈፀሙት ጥፋት 6 ጨዋታ እንዲታገዱ እና በተጨማሪም 5 ሺህ ብር የገንዘብ ቅጣት እንዲከፍሉ የውድድር እና ስነስርዓት ኮሚቴ ውስኗል።
እንዲሁም አሰልጣኝ መሳይ ተፈሪ በዚሁ ጨዋታ በቀይ ካርድ ከሜዳ በተወገዱት ወቅት የዕለቱን 4ኛ ዳኛ ለመማታት መጋበዛቸውን ተከትሎ ጨዋታው ለ3 ደቂቃ እንዲዘገይ ማድረጋቸውን የሚገልጽ ሪፖርት እንዲሁ እንደቀረበባቸው አክሲዮን ማህበሩ ገልጿል።
አሰልጣኙ ለፈፀሙት ጥፋት ተጨማሪ የ4 ጨዋታዎች በድምሩ 10 ጨዋታዎች እንዲቀጡ እና 10 ሺህ ብር የገንዘብ ቅጣት እንዲከፍሉ የውድድር እና ስነስርዓት ኮሚቴ መወሰኑ ታውቋል።
ዘጋቢ፡ ሙሉቀን ባሳ

More Stories
የብሩኖ ፈርናንዴስ መኖሪያ ቤት ተዘረፈ
ክቪቻ ክቫራትስኬሊያ ለስድስት ወራት ከሜዳ ይርቃል
“በአጨዋወታችን ላይ የሚሰነዘረው ሂስ ጥቂቶችን ብቻ የሚወክል ነው” – ሚኬል አርቴታ