አፍሪካ የዓለም አቀፉን የኢነርጂ ሽግግር ታፋጥን ይሆን?
እንደ አልጀዚራ መረጃ አፍሪካ በቢሊየኖች በርሜል ነዳጅ እና በትሪሊየኖች ኪዩቡክ ሜትር ጋዝ ከከርሰ ምድሯ ይወጣል፡፡ ለኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች የሚውሉ የኮባልት እና የማንጋኒዝ ማዕድናት ከፍተኛ አምራችም ናት፡፡
አፍሪካ 125 ቢሊየን በርሜል ድፍድፍ ነዳጅ ክምችትም አላት፡፡ ይህም የዓለምን 7 ነጥብ 2 በመቶ የዓለምን ክምችት ይወክላል፡፡ ከዚሁ ከአፍሪካ ክምችት ሊቢያ እና ናይጄሪያ 70 በመቶውን ይሸፍናሉ፡፡
ሊቢያ 48 ነጥብ 4 ቢሊየን በርሜል ክምችት ሲኖራት፤ ናይጄሪያ ደግሞ 36 ነጥብ 9 ቢሊየን በርሜል ክምችት አላት፡፡ በሶስተኝነት የተቀመጠችው አልጄሪያ 12 ነጥብ 2 ቢሊየን በርሜል፣ እንዲሁም ተከታዩዋ አንጎላ 7 ነጥብ 78 ቢሊየን በርሜል ክምችት አላቸው፡፡
በነዳጅ አምራችነት ደግሞ በአህጉራችን ናይጄሪያን የሚስተካከላት የለም፡፡ ናይጄሪያ በአውሮፓዊያኑ 2024 ያመረተችው ነዳጅ ከአህጉራዊ ምርት 23 በመቶውን የሸፈነ ነው፡፡ አልጄሪያ እና አንጎላ እያንዳንዳቸው 17 በመቶ የአህጉሪቱን የነዳጅ ምርት ሸፍነዋል፡፡
የተፈጥሮ ጋዝን በተመለከተም በ2023 አፍሪካ 18 ትሪሊየን ኪዩቢክ ሜትር የተፈጥሮ ጋዝ ክምችት እንደነበራት ተረጋግጧል፡፡ ከዚህም ውስጥ ናይጄሪያ እና አልጄሪያ 58 በመቶ የሚሆነውን ክምችት ይዘዋል፡፡
ታዲያ እነዚህ ሁሉ ሃብቶች አፍሪካ ነዳጅ እና የተፈጥሮ ጋዝ ላይ ትልቅ አቅም እንዳላት አመላካች ናቸው፡፡ ግን ደግሞ በዚህ ብቻ አያበቃም፡፡ አፍሪካ ለኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች፣ ለባትሪዎች እና ለታዳሽ ኃይል ቴክኖሎጂዎች የሚውሉ ማዕድናት ከፍተኛ አምራችም ናት፡፡
በ2025 የአፍሪካ ሀገራት 71 ነጥብ 2 በመቶ የዓለምን የኮባልት ምርት ሸፍነዋል፡፡ 72 ነጥብ 4 በመቶ የማንጋኒዝ ምርትም የሚመረተው በአፍሪካ ነው፡፡
በሌላ በኩል የአልጀዚራ መረጃ እንደሚያመለክተው በ2024 ኢትዮጵያ እና ዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ የሚያመነጩትን የኤሌክትሪክ ኃይል የሚያገኙት ከታዳሽ ኃይል ነው፡፡ በአፍሪካ ከሚነጨው ኤሌክትሪክ ኃይል በአማካይ 41 በመቶ የሚሆነው ከታዳሽ ኃይል ነው የሚገኘው፡፡
በ2024 6 የአፍሪካ ሀገራት ለዜጎቻቸው ሙሉ በሙሉ የኤሌክትሪክ አቅርቦት ማዳረሳቸው ተረጋግጧል፡፡ አልጄሪያ፣ ግብጽ፣ ሞሪሺየስ፣ ሞሮኮ፣ ሲሸልስ እና ቱኒዚያ በጥቅሉ 215 ሚሊየን ሰዎችን የኤሌክትሪክ ተጠቃሚ አድርገዋል፡፡
የ2024 መረጃ እንደሚያመለክተው በአፍሪካ በአማካይ 63 በመቶ የሚሆነው ሕዝብ የኤሌክትሪክ አገልግሎት ያገኛል፡፡ በአህጉሪቱ ገጠራማ አካባቢዎች ደግሞ አሁንም ሰዎች በኩራዝ፣ ሻማ እና ሌሎች ባትሪዎችን በመጠቀም ነው በጨለማ ጊዜ ብርሃንን የሚያገኙት፡፡
እንደ አጠቃላይ አፍሪካ የዓለም አቀፉን የኢነርጂ ሽግግር የሚያፋጥኑ ከነዳጅና ከተፈጥሮ ጋዝ እስከ ማዕድናት ያሉ የኃይል ምንጮች በስፋት አሏት፡፡ የሚገርመው ግን ከ560 ሚሊየን በላይ ከሰሃራ በታች የሚገኙ ሰዎች የኤሌክትሪክ ኃይል ተጠቃሚዎች እንዳልሆኑ የዓለም ጤና ድርጅት መረጃ ያመለክታል፡፡
የኤሌክትሪክ ኃይል ተጠቃሚ ያልሆኑ የእነዚሁ ሰዎች አሃዝ የዓለምን 86 በመቶ እንደሚሸፍኑ መረጃው ጨምሮ ገልጿል፡፡ በዓለም አቀፍ ደረጃ 655 ሚሊየን ሰዎች ናቸው ከኤሌከትሪክ አገልግሎት ውጪ የሆኑት፡፡
ታዲያ አፍሪካ በማዕድናትም ሆነ በኢነርጂ ባለጸጋ ሆና ሳለ 560 ሚሊየን ሕዝቦቿ ያለ ኤሌከትሪክ ኃይል ተጠቃሚነት መቅረታቸው በእጅጉ የሚያስቆጭ ነው፡፡
ይህንን የአህጉሪቱን ገጽታ ለመቀየር የአፍሪካ ኢነርጂ ሳምንት በየዓመቱ ጉባዔ ይዘጋጃል፡፡ የዘንድሮውም በደቡብ አፍሪካዋ ኬፕታውን ዓለም አቀፍ ኮንቬንሽን ማዕከል በዚህ ሳምንት እየተካሄደ ይገኛል፡፡
የኢነርጂ ሚኒስትሮች፣ ኢንቨስተሮች እና የነዳጅ ኩባንያ ባለሥልጣናት ኬፕታውን ላይ ከትመዋል፡፡ ጉባዔው በዋነኝነት በነዳጅ፣ በተፈጥሮ ጋዝ፣ ኢነርጂን የተመለከተ ፋይናንስ እና የኃይል አቅርቦት እጥረትን መግታት አጀንዳው አድርጓል፡፡ አጀንዳውም በእነዚሁ ጉዳዮች ዙሪያ ያለን ኢንቨስትመንትን የተመለከተ እንደሆነ አልጀዚራ በዘገባው አስፍሯል፡፡
ዘጋቢ፡ ኢያሱ ታዴዎስ

More Stories
የጤና ኤክስቴንሽን ፓኬጅ እየተተገበረ እንደሚገኝ ተገለጸ
ከ22 ነጥብ 5 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ የተደረገባቸው የንብ ቀፎዎች እና የቦንጋ በግ ዝርያዎች ለተጠቃሚዎች ተሰራጭተዋል – የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ግብርና ቢሮ
ጥራት ያለው መረጃን ለህብረተሰቡ ለማድረስ የባለሙያን አቅም ማጎልበት ወሳኝ ነው – በደቡብ ሬዲዮና ቴሌቪዥን ድርጅት የሚዛን ቅርንጫፍ ሥራ አስኪያጅ