ዮርዳን ሄንደርሰን የሳምንቱ ምርጥ ተጫዋች ሆኖ ተመረጠ

ዮርዳን ሄንደርሰን የሳምንቱ ምርጥ ተጫዋች ሆኖ ተመረጠ

የቼልሲው አማካይ ዮርዳን ሄንደርሰን በ6ኛ ሳምንት የኢንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ መርሃ ግብር ቡድኑ በርንማውዝን 5 ለ 1 በሆነ ሰፊ የግብ ልዩነት ባሸነፈበት ጨዋታ ያሳየውን አስደናቂ ብቃት ተከተሎ የሳምንቱ ምርጥ ተጫዋች በመሆን ተመርጧል።

በሊጉ አዘጋጆች በተካሄደው የደጋፊዎች የኦንላይን ድምፅ አሰጣጥ ሄንደርሰን ከፍተኛውን ማለትም 53 በመቶ ድምፅ በማግኘት የበላይነቱን ወስዷል።

በቼልሲ መለያ በሜዳው ስታምፎርድ ብሪጅ የመጀመሪያ ጨዋታውን ያደረገው የ36 ዓመቱ አንጋፋ ተጫዋች፣ የቡድኑን ድል በመምራት ረገድ የአንበሳውን ድርሻ ተወጥቷል።

ጨዋታው እንደተጀመረ በ2ኛው ደቂቃ ላይ ድንቅ የሆነ ግብ በማስቆጠር ቼልሲን መሪ አድርጓል።

ጎል አስቆጥሮ ደስታው ሳያባራ ከአንድ ደቂቃ በኋላ ለሞርጋን ሮጀርስ ሁለተኛዋን ጎል የሚሆን ኳስ አመቻችቶ በማቀበል የቡድኑን የበላይነት አጠናክሯል።

በጨዋታው ማጠቃለያ ላይም ያገኘውን የቅጣት ምት ኳስ በቀጥታ ወደ ግብነት በመቀየር በግል ሁለት ግቦችን በማስቆጠር እና አንድ ግብ የሆነ ኳስ አመቻችቶ በማቀበል ድንቅ ምሽት አሳልፏል።

በዚህም በፕሪሚየር ሊግ ጨዋታ በአንድ ግጥሚያ ላይ በሶስት ግቦች ላይ ቀጥተኛ ተሳትፎ በማድረግ በዕድሜ አንጋፋው የቼልሲ ተጫዋች መሆን ችሏል።

እ.ኤ.አ. በ2022 ክርስቲያኖ ሮናልዶ ለማንቸስተር ዩናይትድ ተጫውቶ ከኖርዊች ሲቲ ጋር በተካተሄደ መርሐግብር ካስመዘገበው ስኬት ወዲህ፣ በአንድ ጨዋታ ሶስት ግቦች ላይ የተሳተፈ በዕድሜ አንጋፋው የሊጉ ተጫዋች ሆኗል።

እንዲሁም ጨዋታው በጀመረ በሶስት ደቂቃዎች ውስጥ ጎል አስቆጥሮ እና አመቻችቶ በማቀበል፣ እ.ኤ.አ. በ1998 ኤሚል ሄስኪ ለሌስተር ሲቲ ከደርቢ ካውንቲ ጋር ባደረገው ጨዋታ ካስመዘገበው ቀጥሎ ሁለተኛው ፈጣን ተጫዋች ሆኖ ተመዝግቧል።

በዚህ የውድድር ዘመን ኮል ፓልመር በመጀመሪያው ሳምንት ከፉልሃም ጋር ባደረገው ጨዋታ የሳምንቱ ምርጥ ተጫዋች ሆኖ ከተመረጠ በኋላ፣ ሄንደርሰን ይህንን ክብር የተቀዳጀ ሁለተኛው የቼልሲ ተጫዋች ሆኗል።

በዚህ ሳምንት ለሽልማቱ በዕጩነት የቀረቡት ኤሊዮት አንደርሰን ከማንቸስተር ሲቲ፣ ዋልተር ቤኒቴዝ ከክሪስታል ፓላስ፣ ኪርናን ዴውስበሪ-ሃል ከኤቨርተን፣ ዳራ ኦሼ ከኢፕስዊች ታውን፣ የሄንደርሰን የቡድን አጋር ጆአኦ ፔድሮ ከቼልሲ እና ቦቢ ቶማስ ከኮቨንትሪ ሲቲ ነበሩ።

ዘጋቢ፡ ሙሉቀን ባሳ