የጤና ኤክስቴንሽን ፓኬጅ እየተተገበረ እንደሚገኝ ተገለጸ
በሽታን በመከላከልና አክሞ በማዳን ላይ ያተኮረው የጤና ኤክስቴንሽን ፓኬጅ በተግባር እየተተገበረ እንደሚገኝ በምስራቅ ጉራጌ ዞን ቡኢ ከተማ አስተዳደር ጤና ጽህፈት ቤት አስታወቀ።
የቡኢ ከተማ አስተዳደር ጤና ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ባህሩ በቀለ እንደገለጹት፤ በከተማ አስተዳደሩ መንግስት ያስቀመጣቸውን የጤና ፖሊሲዎች በተለይም ደግሞ በሽታ መከላከልና አክሞ ማዳንን መሠረት ያደረገ የጤና ኤክስቴንሽን ፓኬጅ ተግባራዊ በመደረግ ላይ ይገኛል።
በከተማ አስተዳደሩ ሶስት ጤና ኬላዎችና አንድ ጤና ጣቢያ እንደሚገኙ ጠቁመው፣ በመንግሥትና መንግስታዊ ባልሆኑ ተቋማት ትብብር ተገንብቶ በ2018 አጋማሽ አገልግሎት መስጠት የጀመረውን የቡኢ ጤና ጣቢያ ቀሪ የህክምና ቁሳቁሶች የማሟላት ሂደቱን ለማጠናቀቅ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመነጋገር ላይ እንደሚገኙም አመልክተዋል።
ሆኖም ግን እንደ ማቀዝቀዣ ያሉ ከፍተኛ የህክምና ማሽነሪዎችን ለማንቀሳቀስ የመብራት ኃይል አስፈላጊ በመሆኑ የመብራት ዝርጋታና አቅርቦት እንዲሁም የመንገድና ትራንስፖርት ችግር ህብረተሰቡን ለእንግልት እየዳረገው እንደሚገኝ አንስተዋል። የሚመለከተው አካልም ለጉዳዩ ትኩረት ሰጥቶ የሰው ኃይልና የመሰረተ ልማት ምደባ እንዲያደርግ ጥሪ አቅርበዋል።
የቡኢ ጤና ጣቢያ ኃላፊ አቶ ሙሉጌታ ሰብስቤ በበኩላቸው፤ ተቋሙ አገልግሎት መስጠት ከጀመረ ጥቂት ወራት ቢቆጠሩም በጤና ጣቢያ ደረጃ ሊሰጡ የሚገባቸውን አገልግሎቶች ሙሉ በሙሉ እየሰጠ ይገኛል ብለዋል።
የድንገተኛ ህክምና፣ የአዋቂዎች ተመላላሽ ህክምና፣ የክሮኒክ ወይም የዘላቂ ህመም ክትትል እንዲሁም የእናቶችና ህፃናት ህክምና አገልግሎቶች በተሟላ ሁኔታ እየተሰጡ ሲሆን የታዘዘውን መድሃኒት የማግኘት ምጣኔም 92 ከመቶ በላይ ነው ብለዋል አቶ ሙሉጌታ።
አገልግሎቱን የበለጠ ተደራሽ ለማድረግ ተጨማሪ የማይክሮስኮፕ፣ የአልትራሳውንድና የኬሚስትሪ ማሽኖች እንዲሟሉላቸው የጠየቁት ኃላፊው፤ ከጤና ጣቢያው አቅም በላይ የሆኑ ህመምተኞች በአቅራቢያው ወደሚገኘው የቡኢ የመጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታል ሪፈር እንደሚደረጉ አመላክተዋል።
በጤና ተቋሙ ህክምና ሲያገኙ ያነጋገርናቸው አቶ ያሬድ ተሻለ እና ወይዘሮ ኤልሳቤት ተስፋዬ በሰጡት አስተያየትም በተቋሙ የሚያገኙት የህክምና እርዳታ ከእንግልት ነፃና መልካም አቀባበል የተሞላበት መሆኑን ገልጸው፤ የመድኃኒት አቅርቦቱም የማህበረሰቡን አቅም ያገናዘበ እንደሆነ መስክረዋል።
ለቀረቡት የመሰረተ ልማት ጥያቄዎች ምላሽ የሰጡት የቡኢ ከተማ አስተዳደር ማዘጋጃ ቤታዊ አገልግሎት ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ሙሉቀን ቱጂ፤ ማዘጋጃ ቤቱ ለጤና ጣቢያው የሚያስፈልጉ መሰረተ ልማቶችን ለማሟላት በቁርጠኝነት እየሰራ እንደሚገኝ ተናግረዋል።
በአሁኑ ወቅት ለጊዜያዊ መፍትሔነት ከፍተኛ አቅም ያለው የሶላር አቅርቦት እየተጠቀሙ እንደሚገኝ የጠቆሙት አቶ ሙሉቀን፤ ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታት በተያዘው የበጀት ዓመት ለጤና ጣቢያውና ለአካባቢው ህብረተሰብ የመብራት አገልግሎት ተደራሽ እንደሚደረግ ገልጸዋል።
በተጨማሪም የመንገድ ትራንስፖርት ችግርን ለመቅረፍ የባጃጅ ስምሪት ከመንገድ ትራንስፖርት ጽህፈት ቤት ጋር በመነጋገር በአጭር ጊዜ ውስጥ ተግባራዊ ይደረጋል ብለዋል።
ዘጋቢ፡ ፍስሃ ክፍሌ – ከወልቂጤ ጣቢያችን

More Stories
አፍሪካ የዓለም አቀፉን የኢነርጂ ሽግግር ታፋጥን ይሆን?
ከ22 ነጥብ 5 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ የተደረገባቸው የንብ ቀፎዎች እና የቦንጋ በግ ዝርያዎች ለተጠቃሚዎች ተሰራጭተዋል – የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ግብርና ቢሮ
ጥራት ያለው መረጃን ለህብረተሰቡ ለማድረስ የባለሙያን አቅም ማጎልበት ወሳኝ ነው – በደቡብ ሬዲዮና ቴሌቪዥን ድርጅት የሚዛን ቅርንጫፍ ሥራ አስኪያጅ