የጉራጌ ሕዝብ ራስ አገዝ ልማት ድርጅት ለአካል ጉዳተኛ ሕፃናት የትምህርት ቁሳቁስ በመደገፍና ግንዛቤ በመፍጠር የመማር መብታቸው እንዲጠበቅ እየሠራ እንደሚገኝ የወልቂጤ ከተማ አስተዳደር ትምህርት ጽ/ቤት ገለፀ።
ድርጅቱ በወልቂጤ ከተማ ድጋፍ ለሚፈልጉ አካል ጉዳተኛ ሕፃናት ተማሪዎች የትምህርት ቁሳቁስና የአካል ድጋፍ አድርጓል።
የወልቂጤ ከተማ አስተዳደር ትምህርት ጽ/ቤት ኃላፊ ወ/ሮ ስሜነሽ ግርማ ድጋፉ በተደረገበት ወቅት እንደገለፁት፤ የ2019 የትምህርት ዘመን ከሕብረተሰቡ ጋር በመቀናጀት በወቅቱ የተጀመረ ሲሆን በትምህርት ለትውልድ ንቅናቄ ለተሞክሮ የሚሆኑ ስራዎች እየተሠሩ ይገኛል።
ተማሪዎችን ወደ ትምህርት ገበታ በወቅቱ በመላክና በትምህርት ቁሳቁስ የተቸገሩ ሕፃናትን በመደገፍ የትምህርት አሰጣጡ በተሻለ ሁኔታ መጀመሩን ገልፀዋል።
ትምህርት ቤቶች ተማሪዎቻቸው የአካቶ ትምህርት ተጠቃሚ እንዲሆኑና ልዩ ፍላጎት ላላቸው ተማሪዎች ትኩረት ተሰጥቶ እየተሠራ መሆኑን የጠቆሙት ወ/ሮ ስሜነሽ፤ የጉራጌ ሕዝብ ራስ አገዝ ልማት ድርጅት አካል ጉዳተኛ ህፃናት ያሉባቸውን ችግሮች በመፍታት ወደ ትምህርት ገበታ እንዲመጡ የተለያዩ ድጋፎችን እያደረገ ነው ሲሉ አያይዘው ተናግረዋል።
የትምህርት ቁሳቁስ በመደገፍና ግንዛቤ በመፍጠር ቤት እንዳይቀሩ በማድረግ እኩል የመማር መብታቸው እንዲጠበቅ ድርጅቱ እየሠራ እንደሆነም አስረድተዋል።
የወልቂጤ ከተማ ሠራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ጽ/ቤት ኃላፊ ወ/ሮ አምሪያ ከድር በበኩላቸው አካል ጉዳተኞች እኩል ተሳታፊና ተጠቃሚ እንዲሆኑ እየተሠራ መሆኑን ጠቁመው፤ የጉራጌ ሕዝብ ራስ አገዝ ልማት ድርጅት አካል ጉዳት ያለባቸው ህፃናት ሕክምናና ትምህርት እንዲያገኙ በማድረግ ማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ችግሮቻቸውን እየፈታ እንደሚገኝ ተናግረዋል።
በመንግሥት ተደራሽ ያልሆኑ ማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ድጋፎችን እየሰጠ መሆኑን አክለው የገለፁት ኃላፊዋ፤ የአካል ድጋፍና ሕክምና እንዲያገኙ እገዛ ስለማድረጉም ጠቁመዋል።
ልዩ ፍላጎት ያላቸውን ሕፃናትን በሕብረተሰቡና በሀገር በቀል ድርጅቶች የመደገፍ ልምድ የሕፃናትን ተሳትፎ ለማሳደግና ሕይወታቸውን ለማቅናት ጠቀሜታው የጎላ ነው ብለዋል።
የጉራጌ ሕዝብ ራስ አገዝ ልማት ድርጅት የፕሮግራምና ፕሮጀክት ክፍል አስተባባሪ አቶ በቀለ መንግስቱ እንደተናገሩት፤ ድርጅቱ ላለፉት ዓመታት በሕፃናት ላይ ትኩረት ያደረጉ ስራዎች ሲሰራ ቆይቷል።
ከፊንላንድ ኤምባሲ ጋር በመሆን ሕፃናት ከትምህርት ገበታ እና ከማህበራዊ ተሳትፎ እንዳይቀሩ እየሠራ መሆኑን ጠቁመው፤ በወልቂጤ ከተማ የአካል ጉዳት ላለባቸው ሕፃናት ሕክምና መርጃ መሳሪያዎችና የትምህርት ቁሳቁስ በመስጠት ቤት እንዳይቀሩ የራሱን ድርሻ እየተወጣ ነው ብለዋል።
ለ108 ሕፃናት የትምህርት ቁሳቁስ ድጋፍ ማድረጋቸውን የገለፁት አቶ በቀለ፤ ትምህርት ቤቶችና መፀዳጃ ቤቶች ለአካል ጉዳተኞች ምቹ እንዲሆኑ ጥረት እየተደረገ መሆኑንም አክለዋል።
አካል ጉዳተኞች እኩል የመጠቀም መብታቸውን መጠበቅ ለሀገሪቱ እድገት አስተዋጽኦው ከፍተኛ መሆኑን ተናግረው፤ የአእምሮ እድገት ውስንነት ላለባቸው ሕፃናት ማእከል ለመክፈት በዝግጅት ላይ መሆናቸውን አቶ በቀለ አስረድተዋል።
ድጋፍ የተደረገላቸው ሕፃናት በሰጡት አስተያየት የትምህርት ቁሳቁስ በማጣት ይቸገሩ እንደነበረና የተደረገላቸው ድጋፍ ከጓደኞቻቸው እኩል በመማር ውጤታማ እንዲሆኑ እንደሚያስችላቸው ተናግረዋል።
ዘጋቢ ፡ ሄኖክ ተክሌ ከወልቂጤ ጣቢያችን

More Stories
ለአፍሪካ ተምሳሌት ከሆነ ምርጫ ወደ መንግሥት ምስረታ!
ትልቅ ሀገር፣ ትልቅ ህዝብ፤ ታላቅ ርዕይ
ትልቅ ሀገር፣ ትልቅ ህዝብ፤ ታላቅ ርዕይ