የጥያ ተስፋና ስጋት

የጥያ ተስፋና ስጋት

በደረሰ አስፋው

ኢትዮጵያ የበርካታ ታሪክ፣ የባህልና ዕድሜ ጠገብ ቅርሶች መገኛ ናት። ቅርስ ትናንትን እያሳየ፣ ዛሬን እየኖረ፣ ነገን እያመላከተ ዘመናትን እንደ ድልድይ የሚያገናኝ ነው። ከትውልድ የሚወረስ መንፈሳዊ እና ቁሳዊ ሃብት ነው። ኢትዮጵያ በተባበሩት መንግስታት የትምህርት፣ የሳይንስና የባህል ድርጅት በዩኔስኮ ዘጠኝ ታሪካዊ ቅርሶችን በማስመዝገብ ከአፍሪካ ግንባር ቀደሟ ሀገር ናት። ከነዚህም ቅርሶች መካከል ውስጥ የጥያ ትክል ድንጋይ አንዱ ነው፡፡

የማንነት መታወቂያና መግለጫ የሆነውን ቅርስ መጠበቅ ደግሞ የእያንዳንዱ ዜጋ ሃላፊነት ነው። ይሁን እንጂ የታሪክ ማህደር የሆነው ቅርስ የሚደረግለት ጥበቃ ምን ይመስላል? ህብረተሰቡስ ለቅርስ ያለው ግንዛቤ ምን ያህል ነው? የሚለው ጉዳይ አሳሳቢ እየሆነ መጥቷል፡፡ እኛም በጥያ ትክል ድንጋይ መካነ ቅርስ ተገኝተን የተመለከትነውን ለአንባቢያን ለማካፈል ወደድን፡፡

የጥያ ትክል ድንጋይ በጉራጌ ዞን ሶዶ ወረዳ ይገኛል፡፡ ጥያ ከአዲስ አበባ 86 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የምትገኝ ከተማ ስትሆን በዓለም አቀፍ ደረጃ የታወቀች ታሪካዊ ከተማ ናት፡፡ የጥያ ትክል ድንጋይ መካነ ቅርስ በጉያዋ የያዘች ከተማ በመሆኗ፡፡ ይህ መካነ ቅርስ ከአዲስ አበባ ወደ ቡታጅራ በሚወስደው መንገድ ጥያ ከተማ በስተግራ 400 ሜትር ያህል ገባ ብሎ በተንጣለለ ሜዳ ላይ ይገኛል። በ15ኛው መቶ ክፍለ ዘመን መካነ ቅርሱን የጎበኙ አጥኝዎችና ተጓዦች ከጉብኝታቸው በኋላ በፃፏቸው መጽሐፍት ኢትዮጵያ በደቡባዊ ክፍሏ በአይነታቸው ለየት ያሉ ከጠፍጣፋ ድንጋይ የተሰሩ ወይም የሜጋሊቲክ ታሪክና ባህል የሚንጸባረቅባቸው ቅርሶች ባለቤት መሆኗን አስታወቁ፡፡ ይህ ምስክርነት የሌሎች አጥኚዎችን ቀልብ በመሳቡ እ.ኤ.አ በ1974 የፈረንሳይ የአርኪዮሎጂ ተመራማሪዎች ወደ ኢትዮጵያ መጥተው ሳይንሳዊ የቅርሶች ምዝገባ እንዲያካሄዱ በር ከፍቷል፡፡

መካነ ቅርሶችን የተመለከተ ጽሁፍ ለህትመት በመብቃቱ ጥያን በዩኔስኮ ልዩ ቦታ እንዲሰጣት እገዛ አድርጓል፡፡ ጥያ በታሪካዊ የድንጋይ ቅርሶቿ እየታወቀች በመምጣቷ እ.አ.አ በ1980 ስሟ በአለም የቅርስ መዝገብ ላይ ሰፈረ። በመካነ ቅርሱ ላይ እ.ኤ.አ በ1982፣ በ1990 እና በ1991 በኢትዮጵያ የሜጋሊቲክ ምሁር የሆኑት ፈረንሳዊ ተመራማሪ ሮዣ ጁሶም እና ኢትዮጵያዊ ተመራማሪ ዶ/ር ካሳዬ በጋሻው የአርኪዎሎጂ ምርምር አካሄዱ። እ.ኤ.አ በ1992 የተገኘውን ውጤት ለመፈተሽ ከተሰራው ስራ በተጨማሪ የላብራቶሪ ትንተናም ተካሂዷል፡፡ ከዚህ በተገኘው መነሻ ሃሳብ መሰረት እ.ኤ.አ በ1995 የመካነ ቅርሱን ምንነት የሚገልጽ ‹‹Tiya L Ethiopia Des Megalithies›› በሚል በፈረንሳይኛ ቋንቋ መጽሐፍ ተጽፏል፡፡

ድንጋዮቹ የቆሙት ከ12 እስከ 14ኛው መቶ ክፍለ ዘመን በነበረው ጊዜ ውስጥ ስለመሆኑ በላቦራቶሪ ፍተሻ ተረጋግጧል፡፡ የጥያ ታሪካዊ ድንጋዮች ከትንሹ 1 ሜትር እስከ ትልቁ 5 ሜትር የሚደርስ የተለያየ ርዝመት፣ ስፋትና ውፍረት አላቸው፡፡ በሀገር ውስጥ በሌሎቹ አካባቢዎች ከሚገኙትና በግብፅ፣ በመካከለኛው ምሥራቅ፣ በሩቅ ምሥራቅ፣ በአውሮፓና በላቲን አሜሪካ እንደታዩት የመቃብር ድንጋዮች አራት ማዕዘን ወይም ድቡልቡል አይደሉም፡፡ በአብዛኛው ከታች ሰፋ ብለው ወደ ላይ እየሾጠጡ የሚሄዱ ናቸው፡፡ በድንጋዮቹ ላይ የተቀረጹት ምስሎችም የጎራዴ ወይም የሰይፍ ወይም የጩቤ፣ የጦር፣ የትራስ እንጨት፣ ክብ ዳቦ ወይም ፀሐይ መሰል ቅርጾች፣ የግማሽ ጨረቃ ምስሎች እጆቹን ወደላይ የዘረጋ ሰው ክንዶች የመሳሰሉት ተጠቃሾች ናቸው፡፡ እነዚህም በአስጎብኛችን የተለያዩ ትርጉም እንዳላቸው ነው የተገለጸልን፡፡ አቶ ሲሳይ ዋቅጅራ የጥያ ትክል ድንጋይ መካነ ቅርስ አስጎብኚ ናቸው፡፡

በመካነ ቅርሱ በአስጎብኝነት ለ10 ዓመታት አግልግለዋል። በትክል ድንጋዩ ላይ ተቀርፀው የሚገኙት ምስሎች የራሳቸው ትርጉም እንዳላቸው ይገልጻሉ። በድንጋዮቹ ላይ ያለው የሰይፍ ብዛት ሟቹ ምን ያህል አውሬ ወይም ጠላት እንደገደለ የሚያሳዩ እንደሆነ ነው የገለጹት። በትክል ድንጋዩ የሚታየው የክብ ቅርጽ ጡት አለያም ደረት መሆኑንም ያስረዳሉ፡፡ ባላ የሚመስል የተቀረጸ ነገር ሁለት ትርጉም ያለው ሲሆን የመጀመሪያው በወቅቱ እንሰትን ለምግብነት ይጠቀሙ እንደነበር የሚገመት ሲሆን ሌላኛው ጊማ ወይም ትራስ ነው የሚሉ እንዳሉ ነው አስጎብኛችን የተናገሩት፡፡ የነጋሪት ምስልም በድንጋዮች ላይ ተቀርጾ ይታያል።

የክርስቲያን ቀብር ነው ተብሎ በተገለጸው በዚህ ቀብር ውስጥ አብሮ ጽናጽል እና ከበሮ መሰል ነገር ተገኝቷል፡፡ ጋሻም በጦርነት ወቅት ሲጠቀሙበት እንደነበር አመላካች ነው፡፡ በቅድመ ታሪክ ይኖሩ የነበሩት ኢትዮጵያዊያን ድንጋዮቹን ለምን እንደተከሏቸው ባይታወቅም የጦር መሪዎች፣ ገዥዎችና ታላላቅ ሰዎች የተቀበሩባቸው ሥፍራዎች ሊሆኑ እንደሚችሉ ይገመታል ሲሉም ገልጸዋል፡፡ ትክል ድንጋዮቹን በተመለከተ አንዳንድ አጥኝዎች 900 ዓመታት እንዳስቆጠሩ ነው የገለጹት፡፡ ሌሎቹ ደግሞ ከቅድመ ታሪክ በፊት በነበሩ ኢትዮጵያውያን የተሠሩ ሊሆኑ እንደሚችሉ ይገምታሉ፡፡ የተወሰኑ ትክል ድንጋዮቹ ለብዙ ዓመታት ሳይወድቁ የቀሩበትን ምክንያት ሲያብራሩም ከመሬት በታች ከ2 ሜትር በላይ በመቀበራቸው እንደሆነ ይገልጻሉ፡፡ “ትራቭል አፍሪካ” የተሰኘው ድረ ገጽ እንደጠቆመውም የጥያ ትክል ድንጋይ የአውሮፓውያንን ዓይን መሳብ ከጀመረ ብዙ ዓመታትን አስቆጥሯል፡፡

ኢጣሊያውያን የአርኪዮሎጂ ባለሙያዎች ጥልቅ ጥናት ባያካሂዱም ኢትዮጵያን በወረሩበት ጊዜ የመጡ ተመራማሪዎች ስለድንጋዮቹ መኖር መረጃ ስለመስጠታቸው የታሪክ ድርሳናት ይጠቁማሉ፡፡ ይሄው ድረ ገጽ በተጨማሪ እንደጠቆመው ወደ ኢትዮጵያ መጥቶ የነበረ አንድ ጀርመናዊ አጥኚም በዚህ ሥፍራ በኩል አልፎ እንደነበረና የጎራዴ ምስል ያላቸው የድንጋይ ትክሎች እንዳየ በጥናቱ አመልክቷል፡ ፡ ከዚህ አጥኚ ቀደም ሲልም ኑቪለ እና ፔር ዛይስ (Neuville and Pere Azais.) የተባሉ አውሮፓውያን ጥያን መጎብኘታቸውን የዩኔስኮ ጥናቶች ያመለክታሉ፡፡ ፊሊፕ በሪግ የተባሉ አጥኚም የጥያ ትክል ድንጋይ ጥንታዊነትን ለዓለም በማስተዋወቅ አዎንታዊ አስተዋጽኦ አበርክተዋል፡፡ የፈረንሳይ አርኪዮሎጂ ባለሙያዎችን መረጃ ዋቢ በማድረግ ከቅርሱ አስጎብኚ እንዳገኘነው የጥያ ትክል ድንጋይ ባለበት ቦታ ዕድሜያቸው ከ18 እስከ 30 የሚገመቱ ብዙ ወጣቶች በጅምላ የተቀበሩበት ሥፍራ እንደሆነ ነው። የአርኪዮሎጂ አጥኚዎች እንደሚሉት የጥያ ትክል ድንጋዮችን ከሰሐራ በታች ካሉ ትክል ድንጋዮች ከአክሱም በስተቀር በዕድሜ የሚበልጣቸው እንደሌለ ነው፡፡

አቶ ሲሳይ ዋቅጅራ በኢትዮጵያ በዓለም ቅርስነት ከተመዘገቡ 13 መካነ ቅርሶች መካከል አንዱ እንደሆነና በ1974 ዓ.ም ተቆፍሮ እንደተጠናም ይጠቅሳሉ። በቁፋሮውም ከ700 እስከ 900 ዓመታት የቆዩ የነገስታቶችና የጦረኞች የቀብር ቦታ እንደሆነና 52 ቅሪተ አካላት በጥናት መረጋገጣቸው ነው የተናገሩት። እነዚህም በሶስት ምድቦች ተከፋፍለው በቅጥር ግቢው ይገኛሉ፡፡ አንዳንዶች ወድቀው የሚገኙ ሲሆን 41 የቁም ድንጋዮች በሁለት ምድቦች ላይ ይገኛሉ፡፡ በጥናቱም 2ቱ ምድቦች የተጠኑ ሲሆን በሶስተኛው ምድብ ላይ የሚገኙት ግን በጥናቱ አለመካተታቸውን ተናግረዋል፡፡ ቅሪተ አካላቱ የተገኙት በወቅቱ ከነበሩ የመገልገያ ቁሶች ጋር መሆናቸው ጠቅሰዋል፡፡

የተደረገው ጥናትም አምሳ አንዱ ቁጭ ብለው የተቀበሩ እንደሆነ ያመለክታል፡፡ የራሳቸው እምነት ያላቸው መሆኑን የሚያመላክት ቢሆንም ይህን አይነት እምነት ይከተሉ ነበር ለማለት ግን እንደማይቻል ነው የጠቆሙት፡፡ ከዚህ ይልቅ ባህላዊ እምነት የሚከተሉ ናቸው ሲሉ ነው የጥናቱን ግኝት ዋቢ በማድረግ የገለጹት፡፡ አንደኛውና ተኝቶ ስለመቀበሩ መረጃው እንደሚያመለክተው ግን ክርስቲያን እንደሆነና በወቅቱ በአካባቢው የክርስትና እምነት ተከታይ እንደነበርም የሚጠቁሙ ጸናጽልና ከበሮ አብረው ስለመገኘታቸው ነው የተናገሩት፡፡ የጥያ ትክል ድንጋይ መካነ መቃብር እስከ 12 ኪሎ ሜትር ከሚገመት ርቀት ድንጋዩን በማምጣት በቀብራቸው ላይ እንደተጠቀሙም ከድንጋዮቹ መረዳት እንደተቻለ ነው አቶ ሲሳይ የተናገሩት፡፡

የተተከሉት ድንጋዮች ከመሬት ውስጥ በሁሉም ትክል ድንጋዮች ሁለት እና ሶስት ቀዳዳዎች አላቸው፡፡ ቀዳዳውም ገመድ አስገብተው እየጎተቱ ወይም ተሸክመው እንዳመጡት የሚያመላክት መሆኑን በመጠቆም፡፡ ከተተከሉት መካነ መቃብሮች መካከል ትልቁ 5 ሜትር እርዝመት አለው፡፡ በጉዳት ምክንያት ሁለት ቦታ ተቆርጦ እንደሚገኝና ለጥናትና ምርምር በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ 6 ኪሎ ግቢ ውስጥ እንደሚገኝ ነው የገለጹት፡፡ ድንጋዩ ጠንካራ ግራናይት ድንጋይ እንደሆነም በጥናት ስለመረጋገጡ ተናግረዋል፡፡ ትክል ድንጋዮቹ እንደ እድሜያቸው የተተከሉ ሲሆን ዝቅተኛ እድሜ ያለው ሟች አነስተኛ ትክል ድንጋይ እና ከፍተኛ ዕድሜ ያለውም ደግሞ ትልቅ ድንጋይ እንደተተከለባቸው ገልጸዋል፡፡ የጥያ ትክል ድንጋይ ለቀጣይ ትውልድ አሻራ የሚጥልም ቅርስ ነው፡፡ የጥንት ሰዎች የስልጣኔያቸው እውቀትንም የሚያመላክቱ ናቸው፡፡ በጥያ ትክል ድንጋይ ታሪኩ እንዳይዛባ በተለያዩ የእውቀት ምንጮችን በመጠቀም መረጃ ማሰባሰቡ ዛሬም እንዳልተገታ አስጎብኛችን ተናግረዋል፡፡ የጥገና ስራዎች ይሰራሉ፡፡ ከእጅ ንክኪ ነጻ እንዲሆኑም ጥበቃ እየተደረገለት እንደሚገኝም ተናግረዋል፡፡ ይሁን እንጂ ታሪካዊ ቅርሱን የሚገልጽ በፈረንሳይኛ የተጻፈ መረጃ እንዳለ ቢገለጽም በአማርኛ አለመተርጎሙ በችግርነት ያነሳሉ። ይህም ተጨማሪ ምርምር ለማድረግና ቅርሱንም ይበልጥ ለማስተዋወቅ እንቅፋት መሆኑ እንዳልቀረ ጠቁመዋል፡፡

በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የሚገኘው የ5 ሜትሩ ጉማጅ በዩኒቨርስቲው ቅጥር ግቢው ተተክሎ የመቆየቱ ሚስጥርም ምን እንደሆነ አያውቁም፡፡ የጥያ ትክል ድንጋይ ቀደም ሲል የበርካታ ጎብኝዎች መዳረሻ ነበር፡፡ አሁን ግን በተቃራኒው ነው የሆነው፡፡ ጎብኝዎች የቆይታ ጊዜያቸውን ለማስረዘም የሆቴል አለመኖር በቅርሱ ጎብኝዎች ላይ ጥላ ያጠላበት እንደሆነ አንስተዋል፡፡ በዚህም አንዳንድ ጎብኝዎች ጥበቃ እየተደረገላቸው ድንኳን ጥለው የሚቆዩ እንዳሉም ነው የተናገሩት፡፡ የጥያ ትክል ድንጋይ አሁን በተደራጁ ማህበራትና በሁለት የጥበቃ ሠራተኞች ብቻ ነው ህልውናው ያለው ማለት ይቻላል። ከማህበሩ አባላትም አብዛኛዎቹ ለቀው ሶስት ብቻ ነው የቀሩት፡፡ መተዳደሪያቸውም ከጎብኝዎች ከሚገኝ 20 ብር ገቢ ነው፡፡ ጎብኚ ካለ እሰየው ከሌለም ወደ ቤተሰብ ጎራ በማለት የእለት ጉርሳቸውን ይቋደሳሉ፡፡ ቀደም ሲል ከፌደራል ቅርስ ጥበቃ ባለስልጣን ስልጠና ያገኙ ነበር፡፡ አሁን ግን ይህም ቆሟል፡፡ ለቅርሱ የሚደረገው እንክብካቤ አናሳ ነው፡፡ ወረዳው፣ ዞኑም ይሁን ክልሉ ቅርሱን እየተመለከቱት አይደለም፡፡

የወዳደቁ ቅርሶች ጥገና አለመደረጉም ሌላው አሳሳቢ ጉዳይ ነው፡፡ በቅርቡ ጠቅላይ ሚኒስትር ደ/ር አብይ አህመድ ከመጽሃፋቸው ሽያጭ ለቅርሱ ሙዚየም ግንባታ እንዲውል ማድረጋቸው ተስፋ ይዞ ቢመጣም የቅርሱ ደህንነት አሁን አሳሳቢ ደረጃ ላይ ስለመገኘቱ የሚያመላክቱ ነገሮች በርካታ ናቸው፡፡ መካነ ቅርሶችን በጋራ ለማልማትና የህብረተሰቡን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ቅንጅታዊ አሰራርን መፍጠር አስፈላጊ ነው ለማለት እንወዳለን፡፡ የኢትዮጵያ ቅርስ ባለስልጣን የሀገሪቷን ባህላዊ እና ታሪካዊ ቅርሶች በመሰነድ ለጥናትና ምርምር እንዲውሉና ለቀጣዩ ትውልድ ማሸጋገር ኃላፊነት አለበት፡፡

ሀገራችን ከዘርፉ የምታገኘውን ጥቅም ለማሳደግና ቅርሶችን ለማልማት የሚያስችሉ የህግ ማዕቀፎችን ማውጣትም ለቅርሶች ደህንነት ዋስትና ይሰጣል፡፡ ቅርሶችን በማልማት የአካባቢውን ማህበረሰብ የኢኮኖሚ ተጠቃሚ ማድረግም የቅርሶቹ ደህንነት እንዲጠበቅ ያደርጋል፡፡ ያለፈውን ዘመን የታሪክ አሻራ እየጠበቅን የሚመጣው ላይ የራሳችንን አሻራ እናሳርፍ፡፡

ቸር እንሰንብት