የልማትና በጎ አድራጎት ድርጅቶች ለተማሪዎች የሚያደርጉት ድጋፍ ለትምህርት ጥራት ውጤታማነት አጋዥ መሆኑ ተገለጸ
የልማትና በጎ አድራጎት ድርጅቶች የመማሪያ ቁሳቁስ አቅርቦት ችግር ላለባቸው ተማሪዎች የሚያደርጉት ድጋፍ የትምህርት ጥራትን ውጤታማ በማድረግ አስተዋጽኦ እንደሚያበረክት ተገለፀ።
ወሄ መያ የልማትና የበጎ አድራጎት ማህበር በጉራጌ ዞን ውስጥ ለሚገኙት ለእኖር፣ እኖር ኤኔር መገር ወረዳዎችና በጉንችሬ ከተማ አስተዳደር ሥር ለሚገኙ ከ850 በላይ ድጋፍ ለሚሹ ተማሪዎች የተለያዩ የመማሪያ ቁሳቁስ ድጋፍ አድርጓል፡፡
የእኖር ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ መብራቱ ተክሌ በዚህ ወቅት እንደተናገሩት፤ የመማር ማስተማር ሂደትን ውጤታማ ለማድረግ በሚደረገው ጥረት የሁሉም ባለድርሻ አካላትን ተሳትፎ ይጠይቃል፡፡
የመማሪያ ቁሳቁስ አቅርቦት ችግር ላለባቸው ተማሪዎች የሚከናወነው ተግባር የትምህርት ጥራትን ለማስጠበቅ ከፍተኛ አበርክቶ እንዳለው ጠቁመው፤ ወሄ መያ የልማትና በጎ አድራጎት ማህበር በዘርፉ የሚስተዋለውን ችግር ለመቅረፍ ለሚያደርገው እገዛ ምስጋና አቅርበዋል፡፡
ማህበሩ በጤናና ሌሎች መሰል ዘርፎች ላይ የሚስተዋሉ የማህበረሠሰቡ ችግሮችን በመለየት የአካባቢው ተወላጆችን በማስተባበር የሚያደርጋቸው ድጋፎች አበረታች በመሆናቸው በቀጣይም ተጠናክረው መቀጠል አለባቸው ብለዋል።
ድጋፍ የተደረገላቸው ተማሪዎችም የተሰጣቸውን የትምህርት ቁሳቁስ በአግባቡ በመጠቀም የተሻለ ውጤት ለማስመዝገብ ትምህርታቸውን በርትተው መከታተል አለባቸው ሲሉ መልዕክት አስተላልፈዋል።
የእኖር እና የእኖር ኤነር መገር ወረዳ ትምህርት ጽ/ቤቶች ሀላፊዎች አቶ ሽኩረታ አብድልከሪም እና አቶ ኤሊያስ ሸምሱ እንደገለፁት፤ መንግስት፣ ባለሀብቱና የበጎ አድራጎት ድርጅቶች በመቀናጀት በትምህርት ልማቱ ዙሪያ ያሉትን ችግሮች ለመቅረፍ እያደረጉት ያለው ተሳትፎ አበረታች ነው።
መንግስታዊና መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች የመማሪያ ቁሳቁስ አቅርቦት ችግር ላለባቸው ተማሪዎች የሚያደርጉት ድጋፍ የትምህርት ጥራትን በማስጠበቅ ረገድ አጋዥ በመሆኑ ተጠናክሮ መቀጠል አለበት ብለዋል።
ወሄ መያ የልማትና በጎ አድራጎት ማህበርም ከ850 በላይ ለሚሆኑ ተማሪዎች ላደረገው ድጋፍ አመስግነው፤ በቀጣይም መሠል በጎ ተግባሩ ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት ተናግረዋል፡፡
የጉንችሬ ከተማ አስተዳደር ትምህርት ጽ/ቤት ሀላፊ አቶ ሀቢብ ናሲር በአንፃሩ፤ ማህበሩ ከትምህርት ቁሳቁስ አቅርቦት በተጨማሪ በየአመቱ የተሻለ ውጤት ላስመዘገቡ ተማሪዎች የሚሰጠው የማበረታቻ ሽልማት ትልቅ ጠቀሜታ እንዳለው ገልፀዋል።
የወሄ መያ የልማትና በጎ አድራጎት ማህበር ምክትል ስራ አስኪያጅ አቶ ደሊል ወርቁ በበኩላቸው፤ ማህበሩ በሃገር ውስጥና ከሃገር ውጪ የሚገኙ የአካባቢው ተወላጆችን በማስተባበር በተገኘው ገንዘብ ድጋፍ እያደረጉ መሆኑን ገልፀው፤ ተግባሩ በቀጣይም ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አስታውቀዋል።
ድጋፍ የተደረገላቸው ተማሪዎችና የተማሪ ወላጆች በበኩላቸው፤ ባገኙት ድጋፍ መደሰታቸው ጠቅሰው፤ በትምህርታቸው ውጤታማ እንዲሆኑ እንደሚያግዛቸው ተናግረዋል።
ዘጋቢ፡ ፉአድ አብደላ – ከወልቂጤ ጣቢያችን

More Stories
ታላቁ የጊፋታ ዋዜማ የሩጫ ውድድር በወላይታ ሶዶ ከተማ ተካሄደ
የቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ስልጠና ተቋማት ቴክኖሎጂን በመቅዳት፣ በማሻሻልና በመፍጠር ለሀገራዊ ዕድገት ከፍተኛ አበርክቶ አላቸዉ – የክልሉ ቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ስልጠና ቢሮ ኃላፊ አቶ አሰፋ ደቼ
የሀዲያ ብሔር ዘመን መለወጫ “ያሆዴ” በዓል ለማክበር የሚመጡ እንግዶችን ለመቀበል በቂ ዝግጅት አድርገናል – የሆሳዕና ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አቶ ሳሙኤል ሽጉጤ