የሀዲያ ብሔር ዘመን መለወጫ “ያሆዴ” በዓል ለማክበር የሚመጡ እንግዶችን ለመቀበል በቂ ዝግጅት አድርገናል – የሆሳዕና ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አቶ ሳሙኤል ሽጉጤ
መስከረም 11 እና 12/2019 ዓ.ም የሚከበረውን የሀዲያ ብሔር ዘመን መለወጫ “ያሆዴ” በዓል ለማክበር ወደ ከተማዋ የሚመጡ እንግዶችን ለመቀበል በሚያስችል መልኩ በቂ ዝግጅት አድርገናል ሲሉ የሆሳዕና ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አቶ ሳሙኤል ሽጉጤ ገለጹ።
ከንቲባው ዝግጅቱን አስመልክተው ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ መስከረም 9/2019 ዓ.ም በነገው ዕለት በከተማ ደረጃ በዓሉ በተለያዩ ዝግጅቶች እንደሚከበር አስታውቀዋል።
የሀዲያ ብሔር ዘመን መለወጫ “ያሆዴ”፣ የክረምቱ ጭጋግና ደመና አልፎ የአዲሱ ዓመት ብርሃን በሚፈነጥቅበት ወቅት በታላቅ ድምቀት የሚከበር ትልቅ በዓል ነው ብለዋል።
ያሆዴ በዓል ከጥንት ጀምሮ ከትውልድ ወደ ትውልድ እየተሸጋገረ የመጣ የህዝብ በዓል እንደሆነና የብሔሩን በርካታ ቱባ ባህሎችን እንደያዘም ካንቲባው ተናግረዋል።
በዓሉ የፊታችን መስከረም 11 እና 12/2019 ዓ.ም በዞን ደረጃ በተለያዩ ዝግጅቶች ታጅቦ የሚከበር በመሆኑ በዓሉን ለማክበር ወደ ሆሳዕና ከተማ የሚመጡ እንግዶችን በክብር ለመቀበል በሚያስችል መልኩ በቂ ዝግጅት ተደርጓል ሲሉ አቶ ሳሙኤል ገልጸዋል።
አያይዘውም የያሆዴን በዓል በማይዳሰስ ቅርስነት በዩኔስኮ ለማስመዝገብ እንቅስቃሴ ላይ እንደሚገኙ ተናግረው፤ ለዚህ አጋዥ የሆኑ በርካታ ስራዎች እንደ ሆሳዕና ከተማ እየተከናወኑ እንደሚገኝ አመላክተዋል።
የያሆዴ በዓል በከተማ ደረጃ በነገው ዕለት ቅዳሜ በኮሎኔል በዛብህ ጴጥሮስ መታሰቢያ አደባባይ እንደሚከበር ያስታወቁት ከንቲባው፤ በያሆዴ ካፕ ሩጫ፣ በያሆዴ ባህላዊ አልባሳት ኤግዚብሽን እና በሌሎችም ባህላዊ ሁነቶች ታጅቦ በደማቁ ይከበራል ብለዋል።
ያሆዴ የእርቅ፣ የአንድነት፣ የፍቅርና የሰላም በዓል እንደሆነና በሰላም የተጀመረው የበዓሉ ድባብ በሰላም እንዲጠናቀቅ በቂ ስራ ስለመሰራቱም ጠቁመዋል።
አክለውም የሆሳዕና ከተማ ሀገራዊና ክልላዊ የሆኑ ትላልቅ ሁነቶችን ባስተናገደችበት ዓመት ማግስት የሚከበር የብሔሩ ታላቅ በዓል በመሆኑ፤ የዘንድሮ ያሆዴ በዓል ከሌሎች ጊዜያት የተለየ ነው ሲሉም ከንቲባው ተናግረዋል።
በመጨረሻም ከንቲባው ለዘንድሮ የሀዲያ ብሔር ዘመን መለወጫ ለያሆዴ በዓል “እንኳን በሰላም አደረሳችሁ” የሚል መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።
በወቅቱም የከተማው የያሆዴ ባህላዊ አልባሳትና ባህላዊ ዕቃዎች ኤግዚቢሽን በከንቲባው ተከፍቷል።
ዘጋቢ: ኤርጡሜ ዳንኤል – ከሆሳዕና ጣቢያችን

More Stories
ታላቁ የጊፋታ ዋዜማ የሩጫ ውድድር በወላይታ ሶዶ ከተማ ተካሄደ
የቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ስልጠና ተቋማት ቴክኖሎጂን በመቅዳት፣ በማሻሻልና በመፍጠር ለሀገራዊ ዕድገት ከፍተኛ አበርክቶ አላቸዉ – የክልሉ ቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ስልጠና ቢሮ ኃላፊ አቶ አሰፋ ደቼ
የልማትና በጎ አድራጎት ድርጅቶች ለተማሪዎች የሚያደርጉት ድጋፍ ለትምህርት ጥራት ውጤታማነት አጋዥ መሆኑ ተገለጸ