ታላቁ የጊፋታ ዋዜማ የሩጫ ውድድር በወላይታ ሶዶ ከተማ ተካሄደ

ታላቁ የጊፋታ ዋዜማ የሩጫ ውድድር በወላይታ ሶዶ ከተማ ተካሄደ

‎በወላይታ ብሔር ዘንድ የሚከበረው የጊፋታ በዓል መዳረሱን ተከትሎ በዋዜማው በዓሉን አስመልክቶ የሩጫ ውድድር ተካሂዷል፡፡

የወላይታ ዞን ዋና አስተዳዳሪ ረዳት ፕሮፌሰር ሳሙኤል ተሰማ የዘንድሮ ጊፋታ በዓል በፓርቲና መንግስት ስራዎች በክልል ደረጃ የተሻለ አፈጻጸም በተመዘገበበት ዓመት መከበሩ ልዩ ያደርገዋል ብለዋል።

‎ዘንድሮ የተጀመረው የጊፋታ ካፕ በየዓመቱ ተጠናክሮ የሚቀጥል መሆኑን ጠቁመው፥ ለዚህም የዞኑ አስተዳደር አስፈላጊውን ድጋፍና ትብብር እንደሚያደርግም አስታውቀዋል።

‎ከመላው ኢትዮጵያዊያን ጋር በመሆን ጊፋታ በዓልን መስከረም 10/2019 ዓ.ም እሁድ ዕለት ለማክበር ሁሉም ሰው የወላይታን ባህላዊ አልባሳት ለብሶ በወላይታ ሶዶ ከተማ ሁለገብ ስታዲየም እንዲገኝ ሲሉ ጥሪያቸውን አስተላልፈዋል።

‎በዓሉ በሠላም እንዲከበር ሁሉም ሰው ለሠላም ዘብ መቆም እንዳለበት ያሳሰቡት ዋና አስተዳዳሪው፥ በተመሳሳይ መልኩ በየአካባቢው ህዝቡ በዓሉን ማክበር እንዳለበትም አመላክተዋል።

‎የወላይታ ሶዶ ከተማ ከንቲባ ወ/ሮ እታገኝ ኃይለማርያም በበኩላቸው፥ ጊፋታ ሩጫ አንድነታችን ይበልጥ የሚጠናከርበትና በዓላችንን ለዓለም የምናስተዋውቅበት ነው ብለዋል።

‎የወላይታ ባህላዊ ጭፈራ የሆነው “ሃያያ ሌኬ”ን ጨምሮ ሌሎች የጊፋታ እሴቶች ለማስተዋወቅ ታላቁ ሩጫ የጎላ ሚና እንዳለውም ተናግረዋል።

‎የዘንድሮ ጊፋታ በዓል በዩኔስኮ በተመዘገበበት ዓመት የሚከበር በመሆኑ በታላቅ ድምቀት ለማክበር ሁሉም ኃላፊነት መውሰድ እንዳለበትም ጥሪያቸውን አቅርበዋል።

‎የወላይታ ዞን ባህልና ስፖርት መምሪያ ኃላፊ አቶ ስምዖን ስላሎ፥ የወላይታ ብሔር ዘመን መለወጫ ጊፋታ በዓል በዩኔስኮ በመመዝገቡ ወላይታን በዓለም ለማስተዋወቅ ትልቅ ሚና አለው ብለዋል፡፡

ዘጋቢ፡ በቀለች ጌቾ – ከዋካ ቅርንጫፍ ጣቢያችን