የጌዴኦ ዞን ምክር ቤት 32ኛ የምክር ቤቶች የጋራ ምክክር ፎረም አካሄደ

በፎረሙ የዞን እንዲሁም የተመረጡ የወረዳ፣ የከተማ አስተዳደር እና የቀበሌ ምክር ቤቶች የ2018 በጀት ዓመት የሥራ አፈጻጸም ሪፖርት ቀርቦ ውይይት ተደርጎበታል።

በውይይቱም በኦዲት ግኝት፣ በገቢ አሰባሰብ የነበሩ ሂደቶች፣ በጤና አገልግሎት እና ትምህርት ቤቶችን ለተማሪዎች ምቹ ከማድረግ እንዲሁም የዞኑ ምክር ቤት የሴክተር መስሪያ ቤቶችንና የታችኛውን የምክር ቤቶች ዕቅድ አፈጻጸም በመገምገም ግብረ መልስ ከመስጠት አኳያ የተሰሩ ሥራዎች በምክር ቤቱ አባላት በጠንካራ ጎን የተነሱ ጉዳዮች ናቸው።

በይርጋጨፌ ከተማ አስተዳደር መዋቅሩ ከተሻሻለ ወዲህ የቀበሌ ምክር ቤት አለመኖሩን በተመለከተ ለተነሳው ጥያቄ ምላሽ የሠጡት የጌዴኦ ዞን ምክር ቤት ዋና አፈ ጉባኤ አቶ ጸጋዬ ታደሰ፤ ከመዋቅር ማሻሻያ ጋር ተያይዞ ያለውን ችግር ለመቅረፍ ከክልሉ መንግሥት እና ከሲቪል ሰርቪስ ኮሚሽን ጋር ተቀናጅተው እየሰሩ መሆናቸውን ተናግረዋል።

በምክክር ፎረሙ የጌዴኦ ዞን ምክር ቤት ከወረዳና ከከተማ አስተዳደር ምክር ቤቶች ጋር የምክር ቤቶችን ተቀናጅቶ የመሥራት አቅም ለማጠናከር የሚያግዝ የጋራ ግብ ስምምነት ተፈራርሟል።

በመጨረሻም የወረዳ፣ የከተማ እና የተመረጡ የቀበሌ ምክር ቤቶች የ2018 በጀት አመት ዕቅድ አፈጻጸም ደረጃ የወጣበት የምዘና ውጤት ለምክር ቤቱ አባላት ቀርቦ የተሻለ አፈጻጸም ላስመዘገቡ ምክር ቤቶች አስፈጻሚ አካላትና ለሶስቱም ቋም ኮሚቴዎች የዕውቅና እና የማበረታቻ ሽልማት ተበርክቶላቸዋል።

ዘጋቢ: እንግዳየሁ ቆሳ – ከይርጋጨፌ ጣቢያችን