ዓለም አቀፉ የቀይ መስቀል ኮሚቴ ደቡብ ሱዳንን አስጠነቀቀ

በአሁኑ ወቅት የምዕራብ፣ የመካከለኛው እና የምስራቅ አፍሪካ ትልቁ የጤና ስጋት የኢቦላ ቫይረስ ስርጭት ሆኗል፡፡ በተለይም በመካከለኛው አፍሪካ የምትገኘው ዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ በኢቦላ ወረርሽኝ እየተፈተነች ነው፡፡

የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ከቀናት በፊት ባወጣው መረጃ እስካሁን ድረስ በዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ 7 ሺህ 200 ሰዎች በኢቮላ ቫይረስ መጠቃታቸው ሲረጋገጥ፣ 3 ሺህ 500 የሚሆኑት ደግሞ የሞት ሰለባ ሆነዋል፡፡

በሀገሪቱ ወረርሽኙን ለመከላከል ከፍተኛ ርብርብ እየተደረገ ቢሆንም ስርጭቱ ግን መንሰራፋቱን ቀጥሏል፡፡ የመንግስታቱ ድርጅትም ከዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ጋር በድንበር የሚዋሰኑና በቅርበት የሚገኙ ሀገራትን ወረርሽኙ ሊስፋፋ ስለሚችል ተገቢውን ጥንቃቄ እንዲያደርጉ አስጠንቅቋል፡፡

ታዲያ ከዚህ መነሻ ዓለም አቀፉ የቀይ መስቀል ኮሚቴ፤ ድንበር ተሻጋሪ የሆነው የኢቦላ በሽታ ከኮንጎ አዋሳኝ በሆነችው ደቡብ ሱዳን ሊከሰት ስለሚችል ጥንቃቄ ማድረግ እንደሚያስፈልግ ማሳሰቡን ሲጂቲኤን (CGTN) ኮሚቴውን ጠቅሶ ዘግቧል፡፡

እስካሁን ድረስ በደቡብ ሱዳን በበሽታው የተጠቃ ሰው እንዳለ የተረጋገጠ ሪፖርት ይፋ አልተደረገም፡፡ ይሁን እንጂ ግጭት በሀገሪቱ በብዛት ስለሚስተዋል የቫይረሱ ስርጭት የሚከሰት ከሆነ በግጭት ለቆሰሉ ሰዎች የሚደረገውን እንክብካቤ ሊያስተጓጉል ይችላል በሚል ነው ቀይ መስቀል ማስጠንቀቂያ አዘል መልዕክት ያስተላለፈው፡፡

በደቡብ ሱዳን የዓለም አቀፉ ቀይ መስቀል ኮሚቴ ተወካይ የሆኑት ዳንየል በንስኮግ ለሲጂቲኤን ሲገልጹ፡-

“ኢቦላ በአሁኑ ወቅት እጅግ አስጊ ሆኗል፡፡ የኮንጎ ድንበር ደግሞ አሁን ከቆምንበት ስፍራ በጣም የቀረበ ነው፡፡ ሰዎች በየቀኑ ቤተሰቦቻቸውንና ወዳጆቻቸውን ለመጠየቅ እንቅስቃሴ ያደርጋሉ፡፡ በዚህም ምክንያት በቫይረሱ ሊጠቁ የሚችሉበት ከፍተኛ አደጋ እንዳይጋረጥባቸው ያሰጋል” ብለዋል፡፡

የቀይ መስቀል ኮሚቴውን የሚያሳስበው የቫይረሱ በደቡብ ሱዳን መከሰት ብቻ አይደለም፡፡

ይልቅስ በሀገሪቱ በተለያዩ ግጭቶች ምክንያት የሚቆስሉ ሕመምተኞች ላይ የሚያደርሰው አደጋ ቀላል የሚባል አለመሆኑም ነው፡፡

በፈረንጆቹ የ2026 6 ወራት ውስጥ የዓለም አቀፉ ቀይ መስቀል ኮሚቴ በደቡብ ሱዳን ግጭት ከተከሰተባቸው አካባቢዎች 266 የቆሰሉ ሰዎችን እንዲሸሹ አድርጓል፡፡ ከ2014 ጀምሮ ደግሞ ከ5 ሺህ በላይ ሕመምተኞች ለአስቸኳይ ቀዶ ጥገና ግጭት ካለባቸው አካባቢዎች እንዲሸሹ ተደርገዋል፡፡

የቀይ መስቀል ኮሚቴው በጦር መሳሪያ ቆስለው ለአስቸኳይ ቀዶ ጥገና የተለዩ ሕሙማን ሕክምና እንዲያገኙ የሚያደርገው በጁባ ወታደራዊ ሆስፒታል ነው፡፡ ሆስፒታሉም በአሁኑ ወቅት ከፍተኛ ጫና ውስጥ ነው የሚገኘው፡፡ ኢቦላ የሚከሰት ከሆነ ደግሞ ጫናው ከቁጥጥር በላይ ሊሆን ይችላል የሚል ስጋት አለ፡፡

በሌላ በኩል የዓለም አቀፉ የቀይ መስቀል ኮሚቴ ሆስፒታል ፕሮጀክት ማናጀር ፓፒ ሉንዱሉካ ኒዪምባታ ለሲጂቲኤን እንደተናገሩት፤ 15 ለዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ቅርበት ያላቸው ሀገራት የኢቦላ ስርጭት አደጋ የተጋረጠባቸው ናቸው ተብለው ተለይተዋል፡፡

ስለዚህም ስጋቱን ለመቀነስ የተሻለ ዕቅድ በመንደፍ ርብርብ ማድረግ እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡

ዘጋቢ፡ ኢያሱ ታዴዎስ