ለስድስት ሺህ ተማሪዎች ከ9 ሚሊየን ብር በላይ በማውጣት ድጋፍ ተደርጓል – የከምባታ ልማት ማህበር

ለስድስት ሺህ ተማሪዎች ከ9 ሚሊየን ብር በላይ በማውጣት ድጋፍ ተደርጓል – የከምባታ ልማት ማህበር

ለስድስት ሺህ ተማሪዎች ከ9 ሚሊየን ብር በላይ በሚሆን ወጪ የመማሪያ ቁሳቁስ ድጋፍ ማድረጉን የከምባታ ልማት ማህበር አስታወቀ።

ልማት ማህበሩ የአካባቢውን ህብረተሰብ ተጠቃሚ የሚያደርጉ የልማት ስራዎችን ከመስራት በተጨማሪ በትምህርት ልማት ላይ በትኩረት እየሰራ መሆኑን አመላክቷል።

በትምህርት ዘርፍ እየመጣ ያለውን ለውጥ በማስቀጠል ለህዝብ ያለውን አጋርነት ለማረጋገጥ በዞኑ በሁሉም መዋቅሮች ለሚገኙ ተማሪዎች የመማሪያ ቁሳቁስ ድጋፍ ለማድረግ 9 ነጥብ 8 ሚሊዮን ብር ወጪ በማድረግ ለ6 ሺህ ተማሪዎች ድጋፍ ማድረጉን የልማት ማህበሩ ዋና ዳይሬክተር አቶ አዲሴ አዳነ ገልፀዋል።

የድጋፍ ስራዎቹ ተማሪዎች ለትምህርት እንዲነሳሱ ከማስቻል ባሻገር የወላጆችን የኢኮኖሚ ክፍተቶችን ለመሸፈን ያለሙ መሆኑን አብራርተዋል።

በአሁን ጊዜም 6 ሺህ ደርዘን ደብተር እና 2 ሺህ ፓኬት እስክርቢቶ በዞኑ ባሉ በሁሉም መዋቅሮች ለሚገኙና በቁሳቁስ ምክንያት ትምህርታቸውን መከታተል ላልቻሉ ተማሪዎች እየተሰራጨ መሆኑን አስገንዝበዋል።

በዱራሜ ከተማ አስተዳደር ለሚገኙ 464 ተማሪዎች የደብተርና የእስክርቢቶ ድጋፍ እንዲሁም በቀዲዳ ጋሜላ ወረዳ በሚገኙ ትምህርት ቤቶች ለሚማሩ 256 ተማሪዎች የመማሪያ ደብተርና እስክርቢቶ ድጋፍ መደረጉን ጠቁመው፤ በዚህ የትምህርት መጀመሪያ ወቅት ሌሎች አካባቢዎች ለሚገኙ ተማሪዎችም የማድረስ ስራዎች ተጠናክረው መቀጠላቸውን ገልፀዋል።

ልማት ማህበሩ በትምህርት ላይ የጀመራቸውን ስራዎች አጠናክሮ እንደሚቀጥል የተናገሩት ዳይሬክተሩ፤ በተለይም በዱራሜ ከተማ የሚገኘውን ‹‹ሂጋ ሞዴል አዳሪ ትምህርት ቤት››ን የልህቀት ማዕከል ለማድረግ የተጀመሩ ውጥኖች ተጠናክረው ይቀጥላሉ ብለዋል።

የትምህርት ልማት ድጋፍ የሰለጠነ ትውልድ ለመገንባት በሚደረግ ጥረት ጉልህ አበርክቶ ያለው መሆኑን ዳይሬክተሩ ገልፀዋል።

አንዳንድ ድጋፍ የተደረገላቸው የተማሪ ወላጆችም ልማት ማህበሩ ያደረገው ድጋፍ ተማሪዎች ትምህርታቸውን እንዲቀጥሉ ከማስቻል ባለፈ በትምህርት ሂደቱ ያላቸውን ተሳትፎ የሚያጠናክር በመሆኑ ደስተኞች መሆናቸውን ገልፀዋል።

በድጋፍ አሰጣጡም የዞኑና የዱራሜ ከተማ አስተዳደር የትምህርት ባለድርሻ አካላት ተገኝተዋል።

ዘጋቢ፡ አለማየሁ ማተቦ – ከሆሳዕና ጣቢያችን