የጌዴኦ ዞን ምክር ቤት 32ኛ የምክር ቤቶች የጋራ ምክክር ፎረም እያካሄደ ነው‎

የጌዴኦ ዞን ምክር ቤት 32ኛ የምክር ቤቶች የጋራ ምክክር ፎረም እያካሄደ ነው


‎ፎረሙ ባለፈው ዓመት በጥንካሬ እና በድክመት የተለዩ ጉዳዮችን በመፈተሽ ድክመቶችን ለማረም እና በጠንካራ ጎን የተለዩ ጉዳዮችን ለማስቀጠል የተዘጋጀ መሆኑ ተመላክቷል።

‎በፎረሙ የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት የዞኑ ምክር ቤት ዋና አፈጉባኤ አቶ ፀጋዬ ታደሰ÷ ፎረሙ ሁሉም በዞኑ ሥር በሚገኙ መዋቅሮች የሚገኙ ምክር ቤቶች ልምድ ልውውጥ የሚያደርግበት መሆኑን ተናግረዋል።

‎አክለውም በተጠናቀቀው በጀት ዓመት ምክር ቤቶችን ከማብቃት አንጻር የአቅም ግንባታ ስልጠና መስጠታቸውን ጠቁመዋል።

‎ለምክር ቤቱ በተሰጠው ስልጣን መነሻ ህግ ማውጣት እና የሚወጡ ህጎች ተፈጻሚነትን በመከታተል የአስፈጻሚ አካላት የክትትል እና ድጋፍ ሥራ በቋሚ ኮሚቴ አማካኝነት መሠራቱን አመላክተዋል።

‎የጌዴኦ ዞን ዋና አስተዳዳሪ ዝናቡ ወልዴ(ዶ/ር) በበኩላቸው÷ ባለፈው አንድ ዓመት ምክር ቤቱ ህግ ከማውጣት ባሻገር የወጡ ህጎች ተፈጻሚነት፣ በዓመቱ የጸደቁ ዕቅዶች ምን ያህል ተግባራዊ መደረጋቸውን እና የህዝብ እርካታ ምን እንደሚመስል በተለያዩ መንገዶች ሲገመግም ቆይቷል ብለዋል።

‎በተለይ የምክር ቤት አባላት የህዝብ ተወካዮች እንደመሆናቸው ህዝቡ የሚያነሳቸውን የልማት እና የመልካም አስተዳደር ችግሮችን ለመቅረፍ እየሠሩ ያለውን ሥራ አጠናክረው መቀጠል እንዳለባቸው አሳስበዋል።

‎በፎረሙ የዞኑ ካቢኔዎች፣ የዞኑ ምክር ቤት አፈ-ጉባኤዎች፣ የሶስቱም ዘርፍ የቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢዎች፣ የወረዳና ከተማ አስተዳደር ምክር ቤት አፈ-ጉባኤዎች እና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ተሳትፈዋል።

‎በፎረሙ በ2018 በጀት ዓመት ከቀበሌ ጀምሮ የህዝብ ምክር ቤቶች ያከናወኑት ተግባራት በሪፖርት ቀርቦ ውይይት እየተደረገ ይገኛል።

‎ዘጋቢ: እንግዳየሁ ቆሳ- ከይርጋጨፌ ጣቢያችን