የላስካ ከተማ ነዋሪዎችን የመሠረተ ልማት ጥያቄ ለመመለስ እየተሰራ መሆኑ ተገለፀ

የላስካ ከተማ ነዋሪዎችን የመሠረተ ልማት ጥያቄ ለመመለስ እየተሰራ መሆኑ ተገለፀ

ባሳለፍነው በጀት አመት የላስካ ከተማ ነዋሪዎችን የመሠረተ ልማት ጥያቄ ለመመለስ የተሰራው ሥራ አበረታች መሆኑን የባስኬቶ ዞን ከተማና መሠረተ ልማት መምሪያ ገለጸ።

መምሪያው በ2018 በጀት ዓመት በተገኙ ስኬቶችና በ2019 ዕቅድ ውስጥ ትኩረት በሚሹ ተግባራት ዙሪያ ከባለድርሻ አካላት ጋር ውይይት አካሂዷል።

የባስኬቶ ዞን ከተማና መሠረተ ልማት መምሪያ ኃላፊ አቶ ክንዴ ፍሬው እንደገለጹ፤ ባለፈው በጀት አመት የአዲስ መንገድ ጠረጋና ከፈታ፣ ነባር ጠጠር መንገዶችን ከመጠገን አንጻር የተሻሉ ሥራዎች ተከናውነዋል።

ላስካ ከተማን በከፊል የፕላን ክለሳ ከማድረግ እና የመኖሪያና የንግድ ግንባታ ፍቃዶችን በፕላን መሠረት እንዲከናወኑ ከማድረግ አንፃር አበረታች ለውጥ መመዝገቡን አመላክተዋል።

ይሁንእንጂ የማዘጋጃ ቤታዊ ገቢዎችን ከመሰብሰብ፤ አዲስ ጠጠር መንገድ ከመሥራትና ድልድዮችን ከመገንባት አንጻር የተሠራው ሥራ ዝቅተኛ እንደነበር አንስተዋል።

በተጠናቀቀው በጀት ዓመት ከግንዛቤ ማነስ ጋር በተያያዘ ያለፈቃድ የሚከናወኑ ሕገ-ወጥ ግንባታዎች እንደነበሩ የገለጹት ኃላፊው፤ የአመለካከት፣ የክህሎትና የአሠራር ውስንነቶን ለመፍታት ልዩ ትኩረት እንደሚሰጥ አመላክተዋል፡፡

በመድረኩ ተገኝተው መልዕክት ያስተላለፉት የባስኬቶ ዞን ዋና አስተዳዳሪ ኢንጂነር በዛብህ ገበየሁ፤ በአዲሱ በጀት ዓመት ለከተማ ኮሪደር ልማት ትኩረት በመስጠት የከተማውን ገጽታ ለማሻሻል የከተማ ውበትን ማሳደግ፣ ለንግድና ኢንቨስትመንት ምቹ ሁኔታ መፍጠር ይጠበቅብናል ብለዋል።

ከተማን ከገጠር ጋር የሚያስተሳስረው የኢኮኖሚ ሰንስለት ጠንካራ መሆን እንዳለበት የጠቆሙት አስተዳዳሪው፤ ለዚህም የገጠር ኮሪደር ልማት የገበሬውን ምርታማነት ከማሳደግ ባለፈ፣ የገጠር ከተሞችን እምቅ አቅም በመጠቀም የከተማና ገጠርን ዘላቂ ልማት ለማረጋገጥ ወሳኝ መሰረት መሆኑን አንስተዋል፡፡

የከተማ መልሶ ማልማት ስራዎች ነዋሪዎችን ተጠቃሚ የሚያደርጉ እና ዘመናዊ መዋቅሮችን የሚከተሉ እንዲሆኑ ማድረግ ከሁሉም የሚጠበቅ ቁልፍ ተግባር መሆን እንዳለበትም መልዕክት አስተላልፈዋል።

አስተዳዳሪው አያይዘውም የሚሠሩ ልማታዊ ተግባራት ግንባታ ብቻ ሳይሆኑ ስራ ዕድል የሚፈጥሩ፣ የኢንቨስትመንት መስህብ የሚያሳድጉ፣ የህዝብን አገልግሎት የሚያሻሽሉና የከተሞችን ቀጣይ እድገት የሚያረጋግጡ እንደሚሆኑ አረጋግጠዋል።

በመድረኩ የመምሪያው የ2018 አፈጻጸም እና የ2019 በጀት አመት ዕቅድ ቀርቦ ትኩረት በሚሹ ተግባራት ላይ ውይይት እየተደረገ ይገኛል።

ዘጋቢ፡- አወል ከድር – አሳውላ ጣቢያችን