የመንግስትን በጀት ለታለመለት አለማ ለማዋል በትኩረት ሊሰራ ይገባል – የካፋ ዞን አስተዳደር

የመንግስትን በጀት ለታለመለት አለማ ለማዋል በትኩረት ሊሰራ ይገባል – የካፋ ዞን አስተዳደር

አስተዳደሩ የ2015 ዓ.ም አፈጻጸም እና የ2016 እቅዱን ገምግሟል ።

የካፋ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ እንዳሻው ከበደ ያለውን ሀብት በአግባቡ ለመጠቀም በዞኑ በጀት እየተሰሩ ያሉ ፕሮጄክቶች በተያዘላቸዉ የጊዜ ገደብ እንዲጠናቀቁ የተለያዩ እንቅስቃሴዎች እየተደረጉ ይገኛል ብለዋል።

በተለይም ለኢንቨስትመንት የሚሆኑ መሬቶችን በአግባቡ በመለየት በዘርፉ ተጠቃሚ ለመሆን መንቀሳቀስ እንደሚያስፈልግ የገለጹት አቶ እነዳሻዉ፤ በከተሞች የገቢ አቅማቸውን በማሳደግ በራሳቸው ገቢ ልማታዊ እንቅስቃሴዎችን ሊከዉኑ ይገባልም ብለዋል።

መምርያዎች የሚያዙ በጀቶችን ለታለመላቸው ዓላማ ለማዋልበትኩረት ሊሰራ ይገባል ብለዋል።

በተጨማሪም በግብርናው ዘርፍ የተስተዋለውን መነቃቃት በማጠናከርና ከወጣቶች ስራ እድል ፈጠራ በማቀናጀት ስራ አጥነትን ለመቀነስ በሚደረገዉ እንቅስቃሴ ዉስጥ መምርያዎች በተሻለ እቅድ ወደ ስራ ሊገቡ እንደሚገባም አሳስበዋል።

በመድረኩ በኢኮኖሚ ማህበራዊና አስተዳደራዊ ዘርፎች የተከናወኑ የመምሪዎች ሪፖርት ቀርቦ ውይይት የተደረገ ሲሆን በተለይም በዞኑ በጀት እየተከናወኑ የሚገኙ የካፒታል ፕሮጀክቶች አፈጻጸም በአብዛኛው መጓተት የሚስተዋልባቸዉ መሆኑ ተገልጿል።

ለአብነትም በገብረ ጻድቅ ሻዎ አጠቃላይ ሆስፒታል ውስጥ እየተገነቡ ያሉት የእናቶች ማቆያና ሴንተራል ላቦራቶሪ ፕሮጄክቶች ግንባታ እና ሌሎችም በተያዘላቸው የጊዜ ገደብ እንዲጠናቀቁ በትኩረት ሊሰራ የሚገባ መሆኑ ተገምግሟል።

በ2015 በጀት አመት ነባርና አዳዲስ ፕሮጄክቶችን ለማከናወን ከ2 መቶ 68 ሚሊዮን ብር በላይ ካፒታል ተይዞ ወደ ስራ የተገባ መሆኑን የገለጹት የካፋ ዞን ፋይናንስና ኢኮኖሚ ልማት መምርያ ሃለፊ አቶ ጥበቡ ገዛኸኝ በበጀት አመቱ በግብርና ሜካናዜሽን እና በወጣቶች ስራ እድል ፈጠራ ሰፋፊ ስራዎች ተሰርተዋል ብለዋል።

በዞኑ ያለዉን ሃብት በተለይም ከቡና ግብይት ከአባቢ ጥበቃና የቱሪዝም መዳረሻዎችን ከማስተዋወቅ አንጻር ያሉ ክፍተቶችን በመቅረፍ የአካበቢዉን አቅም ሊያሳድጉ በሚችሉ ጉዳዮች ላይ በማተኮር ሊሰራ የሚገባ መሆኑን የመድረኩ ተሳታፊዎች አስተያየት ሰጥተዉበታል።

የተነሱ ችግሮችን በመቅረፍ በቀጣይ በጀት አመት የተሻሉ ስራዎችን ለመስራት በቅንጅት መስራት እንደሚያስፈልግ የገለጹት አቶ እንዳሻዉ ተጀምረዉ የተጓተቱ ፕሮጄክቶች በተያዘላቸዉ የጊዜ ገደብ እነዲጠናቀቁ በትኩረት ይሰራልም ብለዋል።

ዘጋቢ: ትዕግስቱ ጴጥሮስ -ከቦንጋ ጣቢያችን