በ2015/16 የምርት ዘመን ለአርሶ አደሩ ለማቅረብ ከታቀደው 15.8 ሚሊየን ኩንታል ማደበሪያ ውስጥ 10 ነጥብ 8 ሚሊየን ኩንታል መሠራጨቱን የግብርና ሚኒስትር ዶክተር ግርማ አመንቴ አስታወቁ

ሀዋሳ፡ ሐምሌ 22/2015 ዓ.ም (ደሬቴድ) በ2015/16 የምርት ዘመን ለአርሶ አደሩ ለማቅረብ ከታቀደው 15.8 ሚሊየን ኩንታል ማደበሪያ ውስጥ 10 ነጥብ 8 ሚሊየን ኩንታል መሠራጨቱን የግብርና ሚኒስትር ዶክተር ግርማ አመንቴ አስታውቀዋል፡፡

በምርት ዘመኑ የ20 ሚሊየን ኩንታል ማደበሪያ ግዢ ፍላጎት ከክልሎች ቀርቦ የ13.6ሚሊዮን ኩንታል ማደበሪያ ግዢ ተፈጽሟል ብለዋል።

ከዚህ ውስጥም 800ሺህ ኩንታሉ ለትግራይ ክልል የሚቀርብ ነው ተብሏል።

ለግዢ የተፈቀደው የውጭ ምንዛሪ በተፈለገው ጊዜ ባለመድረሱ ግዢው ዘግይቶ እንደነበርም ዶክተር ግርማ አውስተዋል።

ለግዢው 1ቢሊየን ዶላር ወጪ ተደርጓል ያሉት የግብርና ሚኒስትሩ ዶክተር ግርማ አመንቴ ግዢው ከአለፈው ዓመት ጋር ሲነጸጸር የ350 ሚሊየን ዶላር ጭማሪ አሳይቷል።

ከአለፈው ዓመት የምርት ዘመን የዞረውን 2 ነጥብ 2 ሚሊየን ኩንታል ማደበሪያ ጨምሮ በጥቅሉ 15 ነጥብ 8 ኩንታል ማደበሪያ ለ2015/16 የምርት ዘመን የመስኖ፣ የበልግና የመኸር እርሻ ልማት ዝግጁ እንዲሆን መደረጉንም ሚኒስትሩ አስታውቀዋል።

ከዚህ ውስጥም 10 ነጥብ 8 ሚሊዮን ኩንታል ማዳበሪያ ለአርሶ አደሮች መሠራጨቱን ሚኒስትሩ በመግለጫቸው አብራርተዋል።

በጅቡቲ ወደብ ለይ የሚገኘው ቀሪ አንድ ሚሊየን ኩንታል ማዳበሪያ እና ሁለት ሚሊየን ተጨማሪ ዩሪያ በአጭር ጊዜ ውስጥ ወደ ሀገር ውስጥ ገብቶ ለአርሶ አደሩ ተደራሽ እንዲሆን የቅርብ ክትትል እየተደረገ እንደሚገኝም ሚኒስትሩ ጠቁመዋል።

በማዳበሪያ ሥርጭቱ ወቅት ከባለፉት ጊዜያት በላቀ መልኩ ህገ-ወጥነትና ሌብነት ታይቷል ብለዋል።

የማደበሪያ እጥረቱን እንደ ምቹ አጋጣሚ በመውሰድ ለግል ጥቅማቸው እያዋሉ በሚገኙት ስግብግቦች ላይ የክልል መንግሥታት ምህረት የለሽ እርምጀ እንደሚወሰድባቸውም ዶክተር ግርማ አስገዝበዋል።

በሥርጭት ወቅት የሚስተዋሉ የማጭበርበር ችግሮችን ለመፍታት የሚያግዙ የዲጅታል ዘዴዎችን በቀጠይ ለመዘርጋት እየታሰበ መሆኑንም አስታውቀዋል።

በሌላ በኩል በምርት ዘመኑ በመኸር እርሻ በዘር ለመሸፈን ከታቀደው 17 ነጥብ 4 ሚሊየን ሄክታር መሬት ውስጥ 10 ነጥብ 5 ሚሊዮን ሄክታሩ በዘር መሸፈኑን ዶክተር ግርማ ጠቁመዋል።

በ2015/16 የምርት ዘመን በዘር ከሚሸፈነው 17 ነጥብ 4 ሚሊየን ሄክታር መሬት 65 ሚሊየን ኩንታል ምርት ለማግኘት መታቀዱንም የግብርና ሚኒስትሩ አመላክተዋል።

ዘጋቢ፡ ጌታሁን አንጭሶ