በአሪ ዞን የባኮ ዳውላ ኣሪ ወረዳ ምክር ቤት ለሁለት ቀናት ሲያካሂድ የቆየውን 4ኛ ዙር 14ኛ ዓመት የስራ ዘመን 18ኛ መደበኛ ጉባኤ ተጠናቀቀ
በአሪ ዞን የባኮ ዳውላ ኣሪ ወረዳ ምክር ቤት ለሁለት ቀናት ሲያካሂድ የቆየውን 4ኛ ዙር 14ኛ ዓመት የስራ ዘመን 18ኛ መደበኛ ጉባኤ፥ የወረዳውን የ2019 ዓ.ም በጀት ከ244 ሚሊዮን ብር በላይ በማጽደቅ አጠናቋል።
በጉባኤው ላይ የተገኙት የአሪ ዞን ሽግግር ምክር ቤት ዋና አፈ ጉባኤ የሆኑት ወ/ሮ ስመኝ ተስፋዬ እንደገለጹት፥ ምክር ቤቶች በህገ መንግስቱ በግልጽ በተደነገገው መሰረት ሕግ አስፈጻሚውንና ሕግ ተርጓሚውን ከመከታተልና ከመደገፍ ባሻገር፥ በህዝብና በመንግስት መካከል ድልድይ በመሆን ለዜጎች ተጠቃሚነት የሚሰሩ አካላት በመሆናቸው በየጊዜው በህዝቡ ዘንድ የሚነሱ የመልካም አስተዳደርና ልማት ጥያቄዎችን ለመፍታት በየደረጃው ካሉ አካላት ጋር በቅንጅት መስራት ይጠበቅባቸዋል ብለዋል።
ጉባኤውም አስቀድሞ የምክር ቤቱን የ17ኛ አመት መደበኛ ጉባኤ ቃለጉባኤ መርምሮ በማጽደቅ ሂደቱን የጀመረ ሲሆን፥ በቀጣይም በወረዳው ምክር ቤት ምክትል አፈ ጉባኤ ወ/ሮ ታሪኳ በኖ የምክር ቤቱ የ2018 አፈጻጸምና 2019 በጀት አመት እቅድ እንዲሁም የወረዳው አስተዳደር የ2018 አፈጻጸምና የ2019 በጀት አመት እቅድ በወረዳው አስተዳደር አቶ መሰረት ቦጋለ ቀርቦ በተሳታፊ የምክር ቤት አባላት ሰፋ ያለ ውይይት ተደርጎበታል።
ከምክር ቤቱ አባላት በተለይም በትምህርት ተደራሽነት፣ በጤና ጉዳዮች፣ የአሪ አፍ መፍቻ ቋንቋን በላቲን ፊደላት የማሳደግ ሂደት ዙሪያ ጥያቄና ሐሳብ ተነስቶ በወረዳው ምክር ቤት ዋና አፈ ጉባኤ አቶ መለሰ ወ/ማርያም በወረዳው ዋና አስተዳዳሪ አቶ መሰረት ቦጋለና ሌሎች የስራ ሀላፊዎች ምላሽና ማብራሪያ ተሰጥቶበታል።
ምክር ቤቱ የወረዳው ፍርድ ቤት የ2018 በጀት አመት ሪፖርትና የ2019 በጅት አመት እቅድ ቀርቦ በጥልቀት መርምሮና ተወያይቶ ያጸደቀ ሲሆን፥ የወረዳው የ2019 በጀት አመት አጠቃላይ የበጀት አዋጅ ረቂቅ በወረዳው ፋይናንስ ጽ/ቤት ሀላፊ በአቶ ምታቸው አረጋ ቀርቦ ካዳመጠና በጥልቀት ከመረመረ በኋላ የ2019 ዓ.ም አጠቃላይ የወረዳው በጀት 244 ሚሊዮን 973 ሺህ 793 ብር መሆኑን በሙሉ ድምጽ በማጽደቅ ጉባኤውን በስኬት አጠናቋል።
የጉባኤው ተሳታፊ የሆኑ የምክር ቤት አባላትም የተመደበው በጀት ለታለመለት አላማ ብቻ እንዲውል በማድረግና የህዝቡን ጥያቄዎች በየደረጃው ለመፍታትና የተሻለ ውጤት ለማስመዝገብ ሁሉም በጋራ ልሰራ እንደሚገባና ድርሻቸውን መወጣት እንዳለባቸው ቃል መግባታቸውን ተናግረዋል።
ዘጋቢ፡ ተመስገን ሰይፉ – ከጂንካ ጣቢያችን

More Stories
ቅምሻ ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) አንደበት፡-
ሳውላ ከተማን ለኢንቨስትመንትና ለቱሪዝም ምቹ የማድረግ የ5 ኪሎ ሜትር የኮሪደር ልማት ሥራ እየተካሄደ ነው
ምሁራን ያላቸውን እምቅ አቅም በመጠቀም ከአካባቢያቸው አልፈው ለሀገራቸው እድገት የበኩላቸውን ሊወጡ እንደሚገባ ተገለጸ