ቅምሻ ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) አንደበት፡-
በለውጡ መንግስት ወደ ሥልጣን የመጡት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር)፤ ከስምንት ዓመታት በላይ በተቆጠረው የሥልጣን ዘመናቸው ለሀገሪቱ ዕድገት በርካታ ተግባራትን አከናውነዋል፡፡
በምጣኔ ሃብት፣ በማህበራዊው፣ በቴክኖሎጂው፣ በፖለቲካው፣ በዲፕሎማሲው እና በሌሎችም ዘርፎች ኢትዮጵያ አስደማሚ የዕድገት ጉዞ እንድታደርግ ያበረከቱት አስተዋጽኦ በጉልህ የሚነሳ ነው፡፡
ታዲያ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በዚሁ የሥልጣን ጉዟቸው የተራመዱትን እርምጃዎችም ሆነ ለዕድገት ይበጃል ያሉትን ጽንሰ ሃሳብ በመጽሃፋቸው ላይ በመከተብ ይታወቃሉ፡፡
በተከታታይነት በርካታ መጽሃፍትን ጽፈው ለአንባቢያን እንካችሁ ማለታቸውም ይታወሳል፡፡
አሁን ደግሞ “ከመስከረም እስከ መስከረም” የተሰኘ ስምንተኛ መጽሃፋቸው በኢ.ፌ.ዴ.ሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ጽ/ቤት አዘጋጅነት ለንባብ በቅቷል፡፡
ይኸው መጽሃፍ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከመስከረም 24 ቀን 2017 ዓ.ም እስከ መስከረም 24 ቀን 2018 ዓ.ም በተለያየ አቅጣጫ ሀገር ለማቅናት በተጓዟቸው ጉዞ ያደረጓቸውን ንግግሮች እና ያስተላለፏቸው መልዕክቶችን ያካተተ ነው፡፡
እኛም በተመረጡ ርዕሰ ጉዳዮች የተመረጡ መልዕክቶችን ለአንባቢዎቻችን በሚመጥን መልኩ በተከታታይነት ለማጋራት እንሞክራለን፡-
ሕዳር 29 ቀን 2017 ዓ.ም የኋሊት እንቃኝ፡- በቱሪስት መናኸሪያዋ አርባ ምንጭ ከተማ 19ኛው የብሄር፣ ብሄረሰቦችና ሕዝቦች ቀን “ሀገራዊ መግባባት ለህብረ ብሄራዊነት” በሚል መሪ ቃል ተካሂዶ ነበር፡፡ በዚሁ ቀን ያስተላለፉትን መልዕክት ጥቂቱን እናካፍላችሁ፡-
“አንድ ሰው መጽሐፍ ሲጽፍ በርካታ መጽሐፍት ማገላበጥ እንዳለበት ሁሉ አንድ ሰው ኢትዮጵያዊ ለመሰኘት እና ኢትዮጵያን ለማወቅ ብዙ ብሄሮችን በጥልቀት ማስተዋል፣ ማጥናት እና መማር ይኖርበታል።
“ኢትዮጵያ ተቀድታ የማታልቅ ባህር ስለሆነች በቁንጽል እውቀት ኢትዮጵያን ዲፋይን ለማድረግ ከመሞከር በየቀኑ ለመማር፣ በየቀኑ ለማቀፍ፣ በየቀኑ ለመቅረብና ለመጠጋት ብንሞክር ይበልጥ የተሻለ እውቀት ለመሰነድ ስለሚያግዝ መላው የኢትዮጵያ ልጆች ኢትዮጵያን አውቀን አልጨረስናትም፡፡
“ብዙ አስደናቂ እውቀቶች፣ ጥበቦች እና ተዝቀው የማያልቁ ሀብቶች ያላት ሀገር ስለሆነች ልባችንን ወደ ፍቅር እና ወደ ሰላም በመመለስ ኢትዮጵያን ለማወቅ እና ለማበልጸግ በጋራ እንድንሰራ በታላቅ ትህትና ጥሪዬን ማቅረብ እፈልጋለሁ፡፡”
“አንድ ሰው ኢትዮጵያዊ ለመሰኘት እና ኢትዮጵያን ለማወቅ ብዙ ብሄሮችን በጥልቀት ማስተዋል፣ ማጥናት እና መማር ይኖርበታል።”
አዘጋጅ፡ ኢያሱ ታዲዎስ

More Stories
በአሪ ዞን የባኮ ዳውላ ኣሪ ወረዳ ምክር ቤት ለሁለት ቀናት ሲያካሂድ የቆየውን 4ኛ ዙር 14ኛ ዓመት የስራ ዘመን 18ኛ መደበኛ ጉባኤ ተጠናቀቀ
ሳውላ ከተማን ለኢንቨስትመንትና ለቱሪዝም ምቹ የማድረግ የ5 ኪሎ ሜትር የኮሪደር ልማት ሥራ እየተካሄደ ነው
ምሁራን ያላቸውን እምቅ አቅም በመጠቀም ከአካባቢያቸው አልፈው ለሀገራቸው እድገት የበኩላቸውን ሊወጡ እንደሚገባ ተገለጸ