ህዝበ ሙስሊሙ የመውሊድ በዓልን ሲያከብር በብዝሃነት ውስጥ የሚንፀባረቁ የመረዳዳትና የአብሮነት በጎ እሴቶችን ይበልጥ በማጠናከር ሊሆን እንደሚገባ ተገለጸ
ሀዋሳ፡ ነሐሴ 18/2018 ዓ.ም (ደሬቴድ) ህዝበ ሙስሊሙ የመውሊድ በዓልን ሲያከብር በብዝሃነት ውስጥ የሚንፀባረቁ የመረዳዳትና የአብሮነት በጎ እሴቶችን ይበልጥ በማጠናከር ሊሆን እንደሚገባ የጉራጌ ዞን እስልምና ጉዳዮች ከፍተኛ ምክር ቤት ሰብሳቢ ሼህ አባስ ያሲን አስገነዘቡ።
ሰብሳቢው ለመላው የእስልምና እምነት ተከታዮች ለ1ሺህ 501ኛው የነቢዩ መሐመድ (መውሊድ) በዓል የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል።
መውሊድ በእስልምና የዘመን አቆጣጠር ዘመነ ሂጅራ ረቢአል አወል የተሰኘው 3ኛው ወር በገባ በ12ኛ ቀን በየዓመቱ ይከበራል።
ይህንን ተከትሎም ዘንድሮ 1ሺህ 501ኛው የነብዩ መሐመድ “ሰለላሁ ዐለይሂ ወሰለም” የልደት በዓል (መውሊድ) በመላ ሀገሪቷ “የፍትሁ ነብይ”በሚል መሪ ሃሳብ በተለያዩ ሀይማኖታዊ ሁነቶች በድምቀት ተከብሮ ይውላል።
በዓሉን አስመልክተው የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት ያስተላለፉት የጉራጌ ዞን እስልምና ጉዳዮች ከፍተኛ ምክር ቤት ሰብሳቢ ሼህ አባስ ያሲን እንዳሉት፥ የነብዩ መሐመድ መወለድ ትልቅ ክስተት ሲሆን በተለይም ለሰው ልጆች ከጨለማ ወደ ብርሃን እንዲያመሩ እንዲሁም ለችግሮች ሁሉ መፍትሄ እንዲሆኑ ዕድልን የፈጠረ ነው።
ታዲያ ነበዩ በመልካም ስብዕናቸው ዕውቅናን የተቸሩ መሆናቸው በመላው ዓለም እንዲወደዱ ስላደረጋቸውም ስማቸው እየነገሰ በየዓመቱ የልደት በዓላቸው ይከበራል ሲሉ ነው የተናገሩት።
ያሁኑ ትውልድ በተለይም ወጣቱ የታላቁ ነቢይ ሙሐመድ (ሰ.ዐ.ወ) ጽኑ አስተምህሮትና ለዓለማት የመላካቸው ምክንያት የሆነውን የእዝነት፣ ይቅርባይነት እና የቸርነት እንዲሁም የመልካም ሰብእና አርአያን በመከተል ለሀገር ሰላም፣ ልማትና ብልፅግና መረጋገጥ የድርሻውን መወጣት እንዳለበት አመላክተዋል።
ህዝበ ሙስሊሙ የመውሊድ በዓልን ሲያከብር የመረደዳት፣ የመደጋገፍ፣ የአብሮነት እና የታመሙትን የመጠየቅ በጎ እሴቶችን ይበልጥ በማጠናከር ሊሆን እንደሚገባ አስገንዝበዋል፡፡
የዘንድሮው የመውሊድ በዓል ከ1 ወር በላይ ሲካሄድ የነበረውን ሀገራዊ ምክክር በስኬት በተጠናቀቀበት ማግስት የሚከበር በመሆኑ ልዩ እንደሚያደርገው የጠቆሙት ሰብሳቢው ለምክክሩ ስኬታማነት አስተዋፅኦ ላበረከቱ አካላት ምስጋናቸውን አቅርበዋል።
ሼህ አባስ በመጨረሻም ለመላው የእስልምና እምነት ተከታዮች በዓሉ የሰላም፣ የልማት፣ የአብሮነት፣ የመከባበር፣ የመተዛዘንና የመረዳዳት እንዲሆንላቸው የእንኳን አደረሳችሁ የመልካም ምኞት መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።
ዘጋቢ፡ መሐመድ ሽሁር – ከወልቂጤ ጣቢያችን

More Stories
የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ብልፅግና ፓርቲ ኃላፊና የየዞን ከፍተኛ አመራሮች በሣውላ ማረሚያ ተቋም አረንጓዴ አሻራቸውን በማኖር ልዩ ልዩ የልማት ሥራዎችን ጎበኙ
በጌዴኦ ዞን ይርጋጨፌ ወረዳ የማህጸን በር ጫፍ ካንሰር ምርመራ እና ልየታ ተካሄደ
በሁሉም ዘርፍ የተመዘገቡ ውጤቶችን በማስቀጠል የምክር ቤት አባላት የበኩላቸውን ሚና ሊወጡ እንደሚገባ ተገለጸ