የአከባቢውን የመሰረተ ልማት ተደራሽነት ለማሳደግ በትኩረት እየሠራ እንደሚገኝ የቡሌ ወረዳ አስተዳደር አስታወቀ

የአከባቢውን የመሰረተ ልማት ተደራሽነት ለማሳደግ በትኩረት እየሠራ እንደሚገኝ የቡሌ ወረዳ አስተዳደር አስታወቀ

መንግስታዊ አገልግሎቶችን በተቀላጠፈ መልኩ መስጠት የሚያስችል በወረዳው የተገነባው የምክር ቤቱ ህንጻም ተመርቋል።

ህግ አውጪ የሆኑ ምክር ቤቶች የዜጎችን ኢኮኖሚያዊ፣ ፖለቲካዊና ማህበራዊ ተጠቃሚነትን በማረጋገጥ በግልጽ የጉባኤ ውይይት ለማድረግ የሚያስችልና መንግስታዊ አገልግሎቶችን በተቀላጠፈ መልኩ ለመስጠት የምክር ቤቱ ሕንጻ መገንባቱ ትልቅ ፋይዳ አለው ያሉት የቡሌ ወረዳ ምክር ቤት ዋና አፈጉባኤ አቶ ዋቆ ሞኮና በህንጻው ምረቃ መደሰታቸውንም ተናግረዋል።

የወረዳው ምክር ቤት ሕንጻ በ2008 ዓ.ም ግንባታው ተጀምሮ በተለያዩ ምክንያቶች ለ7 ዓመታት መጓተቱን ጠቁመው በ2015 ዓ.ም በተወሰደው ቁርጠኛ አመራር ለአዲስ ተቋራጭ በጨረታ በመሰጠቱ መጠናቀቁን የገለጹት አቶ ዋቆ የምክር ቤቱ አባላት በኢኮኖሚያዊ፣ፖለቲካዊና ማህበራዊ ጉዳዮች ላይ ተወያይተው ውሳኔ የሚያሳልፉበት ነው ብለዋል።

የመሰረተልማት ግንባታዎች በታለመላቸው ጊዜ አለመጠናቀቃቸው የሥራ ተቋራጮች ወጣ ገባ ማለት በዋነኝነት የሚጠቀስ ምክንያት ነው ያሉት የቡሌ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ በራቆ በራሶ በ2008 ዓ.ም ተጀምሮ የቆመውን ህንጻ ወረዳው ከፍተኛ የሆነ የበጀት ችግር ባለበት ከአከባቢው ገቢ በመሰብሰብ እና ከክልልና ከፌዴራል የሚመጡ የጋራ ገቢዎችን በማጣመር ተጠናቆ ለአገልግሎት እንዲበቃ መደረጉን ተናግረዋል።

አስተዳዳሪው አክለውም ከዚህ ቀደም ተወዝፈው የቆዩ ግንባታዎችን በማጠናቀቅ ለአዳዲስ የመሰረተ ልማት ግንባታዎች መዘጋጀታቸውን አስረድዋል።

ምክር ቤቱ ሉዓላዊ የስልጣን ባለቤት ነው ያሉት የጌዴኦ ዞን ምክር ቤት ዋና አፈጉባኤ ወ/ሮ ምስጋና ዋቃዮ ማንኛውም የመሰረተልማት ጥያቄዎች የሚጠየቁበት ምክር ቤቱ፥ ከዚህ ቀደም ምቹ ባልሆነ ቦታና ሁኔታ በከኪራይ ቤት መንግስታዊ አገልግሎቶችን ሲሰጥ የቆየው የቡሌ ወረዳ ምክር ቤት ዛሬ ላይ ለራሱ ህንጻ መብቃቱ አስደሳች መሆኑን ገልጸዋል።

በጌዴኦ ዞን ተጀምረው ለዓመታት የቆዩ የመሰረተልማት ግንባታዎችንም የማጠናቀቁ ሥራ በየአካባቢው እየተሠራ እንዳለም ወ/ሮ ምስጋና አንስተዋል።

የፌዴራልና የክልል የህዝብ ተወካዮች፣ የቡሌ ወረዳ የህዝብ እንደራሴዎች፣ የዞንና የወረዳ አመራሮች እንዲሁም የተለያዩ ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች በምረቃው መርሃግብሩ ላይ ተሳትፈዋል።

ዘጋቢ ፡ ውብሸት ከሣሁን ከፍስሐገነት ጣቢያችን