በማህበረሰብ አቀፍ ጤና መድህን ከ900 ሚሊዮን ብር በላይ የሚሆን ሀብት መሰብሰብ መቻሉ ተገለጸ

በማህበረሰብ አቀፍ ጤና መድህን ከ900 ሚሊዮን ብር በላይ የሚሆን ሀብት መሰብሰብ መቻሉ ተገለጸ

ሀዋሳ፡ ሰኔ 19/2018 ዓ.ም (ደሬቴድ) በማህበረሰብ አቀፍ ጤና መድህን ከ900 ሚሊዮን ብር በላይ የሚሆን ሀብት ማሰባሰብ መቻሉን የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ጤና ቢሮ አስታወቀ፡፡

‎በጤናው ዘርፍ የማህበረሰብ ተሳትፎን በማጠናከር ተጠቃሚነትን ለማሳደግ ቅንጅታዊ አሰራርን ለማጠናከ እየሰራ እንደሚገኝ ተመላክቷል።
‎‎
‎የኢፌዲሪ ጤና ሚኒስትር ሚኒስቴር ዴኤታ ከፍተኛ አማካሪ ዶ/ር ያሬድ አግደው፥ የሪፎርሙ አስፈላጊነት ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎች፣ ሰው ሰራሽና የተፈጥሮ አደጋዎች በመጨመራቸው መከላከልን ትኩረት ያደረገ ሥርዓት መዘርጋት በማስፈለጉ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡

‎ነባራዊ ሁኔታን መቋቋም የሚችልና የማይበገር የጤና ሥርዓትን ለመዘርጋት የጤና ሪፎርሙ አስፈላጊነት የጎላ መሆኑንም ዶ/ር ያሬድ አክለዋል ።

‎የማህበረሰብ ተሳትፎን በማጠናከር የህብረተሰቡን ተጠቃሚነት ማሳደግ፣ ቅንጅታዊ አሰራርን በተለይ ድጋፍና ክትትል፣ የትምህርት ዕድል እና የትርፍ ሰዓት ክፍያን ጨምሮ ሌሎች ጉድለቶችን ለማረም በጋራ መስራት ይጠበቅብናል ያሉት ደግሞ የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ጤና ቢሮ ኃላፊ አቶ እንዳሻው ሽብሩ ናቸው።

‎በሀገር ደረጃ የተጀመሩ የሪፎርም ተግባርን ከዳር ለማድረስ እና የተጣለውን ግብ ለማሳካት ሁሉም አካል የበኩሉን ሊወጣ እንደሚገባ አሳስበዋል ።

‎በጤናው ዘርፍ የቴክኖሎጂ አጠቃቀምን በማሳደግ ባህላዊ የወረቀት አሰራርን ደረጃ በደረጃ በማስቀረት የህክምና ፍሰትን ፈጣንና ሚስጥራዊነቱ የተጠበቀ እንዲሆን መቻሉን ጠቁመዋል።

‎የሪፎርሙ መተግበር የእናቶችን ሞት ከመቀነሱም ባሻገር የህፃናት የጤና ሁኔታ በከፍተኛ ደረጃ ተሻሽሏል ያሉት ኃላፊው፥ የሰው ልጆች የመኖሪያ ጣሪያ ወደ 68 ዓመት ማደጉን አብራርተዋል ።

‎በማህበረሰብ አቀፍ ጤና መድህን ኘሮግራም ወደ 900 ሚሊዮን የሚሆን ሀብት መሰብሰብ መቻሉን የጠቆሙት አቶ እንዳሻው፥ ከውጪ የሚገባ ክትባትና መድሀኒትን ማማምረት መጀመሩ በዘርፉ የነበረውን ሽፋን በከፍተኛ ሁኔታ ማሳደግ መቻሉንም ተናግረዋል ።

‎በክልሉ በሚገኙ 1 ሺህ 300 የጤና ኬላዎች በርካታ ተግባራት እየተከናወኑ እንደሚገኝ ገልጸው፥ በቀጣይም ለህብረተሰቡ በቂ ህክምና እንዲሰጡ በትኩረት እንደሚሰራ አረጋግጠዋል ።

‎የመድረኩ ተሳታፊ ከሆኑት መካከል የቦረዳ ወረዳ ጤና ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ዳዊት ዳርጫና አቶ አያለው በላይነህ አሪ ዞን የገሊላ ከተማ አስተዳደር ጤና ዩኒት መሪ ሲሆኑ ሥርዓትን ለመዘርጋት የጤና ሪፎርሙ አስፈላጊነት የጎላ በመሆኑ ለተግባራዊነቱ ግብዓት የሚሆን መድረክ መሆኑን ገልጸዋል ።

‎ለ ሁለት ተከታታይ ቀናት በቆየው ምክክር መድረክ የክልል ፣ የዞን እና የከተማ አመራሮችን ጨምሮ የዘርፉ ባለሙያዎች ተሳታፊ ሆነዋል።

‎ዘጋቢ ፡ ተመኙህ ገረሱ – ከአርባምንጭ ጣቢያች