በጎፋ ዞን ወጣቶች በጎ ፈቃድ አገልግሎት የበጋ ማጠቃለያና የክረምት በጎ ስራ ማስጀመሪያ መረሃ-ግብር ተካሄደ
ሀዋሳ፡ ሰኔ 19/2018 ዓ.ም (ደሬቴድ) በጎፋ ዞን ወጣቶች በጎ ፈቃድ አገልግሎት የበጋ ማጠቃለያና የክረምት በጎ ስራ ማስጀመሪያ መረሃ-ግብር በጋልማ ከተማ አካሂዷል፡፡
በክረምቱ ወቅት 148 ሺ ወጣቶችን በማሳተፍ 430 ሺ የህብረተሰብ ክፍሎችን ተጠቃሚ ለማድረግ እየተሰራ መሆኑን የወጣቶችና በጎ ፈቃድ አገልግሎት ጽ/ቤት አስታውቋል።
”በጎነት ለኢትዮጵያ ከፍታ” በሚል መሪ ቃል በጎፋ ዞን በዞናዊ የክረምት በጎ ስራ ማስጀመሪያ በአንዲት አቅመ ደካማ እናት የቤት ግንባታ ስራ በጋልማ ከተማ ተጀምሯል።
የጋልማ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ኢንጂነር ተስፋለም ነከረ፤ በከተማዋ የአቅመ ደካማና የገቢ አቅም የሌላቸው ግለሰቦች የልየታ ስራ መሰራቱንና በዚህም ክረምት በዞኑ ድጋፍ የአንዲት እናት ቤት ደረጃውን በጠበቀ መልኩ መስራት መጀመሩን ተናግረዋል።
የጎፋ ዞን ዋና አስተዳደር ኢጂነር ዳግማዊ አየለ በበኩላቸው፤ የተቸገሩትን መርዳት የኢትዮጵያዊነት ባህላችን ከመሆኑም ባሻገር አብሮ የመበልጸግና የማደግ መርህን መከተል ከፈጣሪ የሚገኝ ትልቅ ተግባር መሆኑን ገልጸዋል።
የመንግስት ተቋማትና ባለሀብቶች፣ ወጣቶችና የሀይማኖት ተቋማት አቅመ ደካማ ወገኖቻችንን መደገፍ ከፈጣሪ የሚሰጥ ጸጋ መሆኑን እንዲሁም፤ የህሊና እርካታን የሚሰጥ ክንውን በመሆኑ ማህበረሰቡ የተለመደውን ትብብር እንዲያደርግ ጥሪ አቅርበዋል።
ሁሉንም የህብረተሰብ ክፍሎች በማሳተፍ በክረምት ወራት ደረጃቸውን የጠበቁ ቤቶች መገንባት እንደሚገባ አሳስበዋል።
የጎፋ ዞን ወጣቶችና በጎ ፍቃድ አገልግሎት መምሪያ ኃላፊ አቶ ብረሃኑ ደቻሳ፤ በበጋው ወቅት በ18 የሥራ መስኮች ውጤታማ መሆናቸውን አንስተው በክረምቱ ወቅትም 148 ሺ ወጣቶችን በማሳተፍ 430ሺ የህብረተሰብ ክፍሎችን ተጠቃሚ በማድረግ ከ280 ሚሊየን ብር በላይ የሚሆነውን ወጪ ለማስቀረት መታቀዱን ተናግረዋል፡፡
ድጋፍ የተደረገላቸው አቅመ ደካማ እናት የገቢ አቅም እንደሌላቸውና ለረዥም ጊዜ መቸገራቸውን አንሰተው፤ ቤትና የቤት ቁሳቁስ ለሟሟላት ለተደረገው ድጋፍ የዞኑን መንግስት አመስግነዋል፡፡
በዕለቱ “አንድም ዜጋ በደም ዕጦት እንዳይሞት በበጎ ፈቃድ ድርሻችን እንውጣ” በሚል መሪ ቃል የደም ልገሳ በማድረግ መረሃ-ግብሩ ተጠናቋል።
ዘጋቢ፡ ሰንታየሁ ሙላቱ – ከሳውላ ጣቢያችን

More Stories
ህዝበ ሙስሊሙ የመውሊድ በዓልን ሲያከብር በብዝሃነት ውስጥ የሚንፀባረቁ የመረዳዳትና የአብሮነት በጎ እሴቶችን ይበልጥ በማጠናከር ሊሆን እንደሚገባ ተገለጸ
የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ብልፅግና ፓርቲ ኃላፊና የየዞን ከፍተኛ አመራሮች በሣውላ ማረሚያ ተቋም አረንጓዴ አሻራቸውን በማኖር ልዩ ልዩ የልማት ሥራዎችን ጎበኙ
በጌዴኦ ዞን ይርጋጨፌ ወረዳ የማህጸን በር ጫፍ ካንሰር ምርመራ እና ልየታ ተካሄደ