በክረምት በጎ ፍቃድ አገለግሎት ሁሉም የህብረተሰብ ክፍሎች ተሳትፎ በማድረግ የበኩላቸውን እንዲወጡ የዞኑ መምሪያ አስታወቀ

በክረምት በጎ ፍቃድ አገለግሎት ሁሉም የህብረተሰብ ክፍሎች ተሳትፎ በማድረግ የበኩላቸውን እንዲወጡ የዞኑ መምሪያ አስታወቀ

ሀዋሳ፡ ሐምሌ 15/2015 ዓ.ም (ደሬቴድ) በክረምት በጎ ፍቃድ አገለግሎት ሁሉም የህብረተሰብ ክፍሎች ንቁ ተሳትፎ በማድረግ የበኩላቸውን እንዲወጡ የጌዴኦ ዞን ወጣቶችና ስፖርት መምሪያ አስታውቋል፡፡

የ2015 ዓ.ም የክረምት በጎ ፍቃድ አገልግሎት በጌዴኦ ዞን ዲላ ዙሪያ ወረዳ በይፋ ተጀምሯል፡፡

በመክፈቻ ሥነ-ስርዓቱ ላይ የወረዳው ወጣቶችና ስፖርት ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ታረቀኝ በቀለ በዘንድሮ ክረምት በጎ ፍቃድ አገልግሎት ሥራ ከ25ሺህ 7 መቶ በላይ ወጣቶችን በማሳተፍ ከ72ሺህ 8 መቶ በላይ የተለያዩ ድጋፍ የሚሹ የህብረተሰብ ክፍሎችን ተጠቃሚ ለማድረግ መታቀዱን አስረድተዋል፡፡

በባለፈው ዓመት የአቅመ ደካሞችን፣ የዘማች ቤተሰቦችንና የአረጋዊያንን ቤት ገንብተው ማስረከባቸውን የገለጹት ኃላፊው በተያዘው በጎ ሥራ 2 መቶ 88 ቤቶች ግንባታ ሥራን ጨምሮ በ15 ችግር ፈቺ ተግባራት በማሰማራት ከ20 ሚልዮን ብር በላይ ገንዘብ ለማዳን መታቀዱንም አብራርተዋል፡፡

የዲላ ዙሪያ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ተገኝ ታደሴ በባለፈው ዓመት በወጣቶች ክረምት በጎ ፍቃድ አገልግሎት በረካታ ተግባራት ማከናወናቸውን ጠቅሰው በዘንድሮ በጎ አገልግሎት ሥራ በእጥፍ ለማሳደግ እየተሠራ መሆኑን ገልጸዋል።

በ2014/15 በክረምት በጎ ፍቃድ አገልግሎት በአንድ ጀንበር 41 የአቅመ ደካሞችን ቤት ተሰርተው እንደነበር የገለጹት አቶ ተገኝ በዘንድሮው በክረምት ሥራ 133 አዳዲስና 95 ቤቶችን በመጠገን በአጠቃላይ 2 መቶ 88 ቤቶችን ለመጠገን አቅዶ በዛሬው ዕለት መጀመራቸውን ተናግረዋል፡፡

የጌዴኦ ዞን ወጣቶችና ስፖርት መምሪያ ኃላፊ አቶ ደግነት ሀይሉ በዞኑ በባለፈው ዓመት ከ9 መቶ በላይ የአቅመ ደካሞች ቤት ግንባታና የተለያዩ ተግባራት ማከናወናቸውን በመጠቆም በድርቅ ለተጎዱ አከባቢዎችን የመደገፍ ሥራ ማከናወናቸውን ተናግረዋል፡፡

የዲላ ዙሪያ ወረዳ በሁሉም ዘርፎች ግንባር ቀደም በመሆን ውጤታማ ሥራዎችን እያከናወነ መቆየቱን የገለጹት አቶ ደግነት በዘንድሮው አመትም በዞን ደረጃ በተመረጡ በ15ቱም ዘርፎች የበለጠ መፈፀም አለባቸው ብለዋል፡፡

ሁለተናዊ ብልጽግና ለማረጋገጥ በሚደረገው ርብርብ ከወጣቱ ባለፈ ሁሉም የህብረተሰብ ክፍሎች የነቃ ተሳትፎ በማድረግ ለመርሃ-ግብሩ ስኬታማነት የድርሻቸውን እንዲወጡ አሳስበዋል፡፡

በመክፈቻ ሥነ-ስርዓት የአቅም ደካሞች ቤት ሥራ፣ የችግኝ ተከላ፣ የምግብና የትምህርት ቁሳቁስ ድጋፍ የተደረገ ሲሆን በባለፈው በጎ ሥራ የጎላ አስተዋጽኦ ላበረከቱ ወጣቶችና ባለድርሻዎች የምስጋናና የእውቅና ምስክር ወረቀት ተበረከተላቸዋል፡፡

ዘጋቢ፡ እምነት ሽፈራው – ከፍስሀ ገነት ጣቢያችን