የአንድ ሀገር ሁለንተናዊ እድገትና የወደፊት እጣ ፈንታ የሚወሰነው ሁሉን አቀፍ የትምህርት ጥራት በማረጋገጥ መሆኑ ተገለጸ

የአንድ ሀገር ሁለንተናዊ እድገትና የወደፊት እጣ ፈንታ የሚወሰነው ሁሉን አቀፍ የትምህርት ጥራት በማረጋገጥ መሆኑ ተገለጸ

ሀዋሳ፡ ሰኔ 18/2018 ዓ.ም (ደሬቴድ) የአንድ ሀገር ሁለንተናዊ እድገትና የወደፊት እጣ ፈንታ የሚወሰነው ሁሉን አቀፍ የትምህርት ጥራት በማረጋገጥ መሆኑን የኢፌዴሪ ጉምሩክ ኮሚሽን ኮሚሽነር ደበሌ ቃበታ (ዶር) ገለጹ፡፡

ኮሚሽነሩ ይህን ያሉት ወልቂጤ ዩኒቨርሲቲ በተለያዩ የትምህርት መስኮች ያሰለጠናቸውን 363 ተማሪዎቹን ለ17ኛ ጊዜ ባስመረቀበት ወቅት ነው፡፡

በምረቃ ሥነ-ሥርዓቱ ላይ የተገኙት የኢፌዴሪ ጉምሩክ ኮሚሽን ኮሚሽነር እና የወልቂጤ ዩኒቨርሲቲ ስራ አመራር ቦርድ ሰብሳቢ ደበሌ ቃበታ(ዶር)፥ የሀገራት ሁለንተናዊ እድገትና የወደፊት እጣ ፈንታ የሚወሰነው ጠንካራ የትምህርት መዋቅር፣ ሁሉ አቀፍ የትምህርት ጥራትና በክህሎት የዳበረ ትውልድን በመቅረጽ መሆኑን አስታውቀዋል።

ሀገራችን ኢትዮጵያ ካለችበት ነባራዊ ሁኔታ አንጻር ተለዋዋጭና ተገማች ያልሆነው አለም አቀፋዊ ለውጥ ለመቋቋም ተመራቂዎች ከተቀጣሪነት ስነልቦና ወጥተው የስራ ዕድል ፈጣሪነት አስተሳሰብ ማጎልበት ይጠበቅባቸዋል ነው ያሉት።

ወልቂጤ ዩኒቨርሲቲ በኢትዮጵያ ውስጥ ካሉ የተግባራዊ ሳይንስ ዩኒቨርሲቲዎች መካከል አንዱ መሆኑና ተመራቂዎችም የቀሰሙትን ሁለንተናዊና በስራ የተፈተነ ዕውቀት ቀጣይ በሚገጥማቸው በየትኛውም የስራ መስክ ብርቱ ተወዳዳሪ እንደሚያደርጋቸው አስታውቀዋል።

የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንት አብድልሙህሲን ሀሰን(ዶ/ር) እንዳሉት፥ በዩኒቨርሲቲው ትምህርታቸውን ሲከታተሉ የቆዩ 355 በመጀመሪያ ዲግሪ እና 8 በሁለተኛ ዲግሪ በአጠቃለይ 363 ሰልጣኞች መመረቃቸውና ዩኒቨርሲቲው በትምህርት ሚኒስቴር ከተጀመሩት የትምህርት ጥራት ማሻሻያ ሪፎርሞች ጋር እራሱን በማናበብ 92.5 ከመቶ የሚሆኑ ተማሪዎች የመውጫ ፈተና ማሳለፉን አስረድተዋል።

በዩኒቨርሲቲው የመማር-ማስተማር ሂደቱን ዘመናዊና በተግባር የተደገፈ ለማድረግ በርካታ ስራዎች መከናወናቸውን ገልጸው፥ ከዚህ በተጨማሪም በዘንድሮው ዓመት የቡታጅራ ካምፓስን እውን በማድረግ መደበኛ የመማር ማስተማር ስራ በይፋ ተጀምሯል ብለዋል።

የዩኒቨርሲቲ ማህበረሰቡን መሰረት ያደረጉ ምርምሮችና የቴክኖሎጂ ሽግግር ፕሮጀክቶች ተጀምረዋል ያሉት ፕሬዝዳንቱ፥ በርካታ የማህበረሰብ አገልግሎት ፕሮጀክቶች እየተተገበሩ መሆናቸውን ተከትሎ የአጠቃላይ ትምህርት ዘርፉን ጥራትን ለመደገፍ በ20 የዩኒቨርሲቲው ካችመንት ማዕከላት ለሚገኙ ተማሪዎች ለ45 ቀናት በግቢው ውስጥ በማቆየት የማጠናከሪያ ትምህርት እንዲሰጣቸዉ ተደርጓል ብለዋል።

ባርኮት ሀይሉ የህግ እና ባስኔል ጌቱ የሶፍት ዌር ኢንጂነሪንግ ትምህርት ክፍል ተመራቂዎች በሰጡት አስተያየት፥ ጥረታቸው ፍሬ አፍርቶ ለምርቃት በመብቃታቸው መደሰታቸውን ገልጸው በሙያቸው ማህበረሰቡን ለማገልገል መዘጋጀታቸውንም አስታውቀዋል።

ዘጋቢ: መላኩ ንማኒ – ከወልቂጤ ጣቢያችን