ሕብረተሰቡ የሚያነሳቸውን ጥያቄዎች በአግባቡ ለመመለስ ባለድርሻዎች በቁርጠኝነት መሥራት እንደሚገባቸው ተገለጸ

ሕብረተሰቡ የሚያነሳቸውን ጥያቄዎች በአግባቡ ለመመለስ ባለድርሻዎች በቁርጠኝነት መሥራት እንደሚገባቸው ተገለጸ

‎የኮቾሬ ወረዳ ምክር ቤት 4ኛ ዙር 37ኛ መደበኛ ጉባኤ አካሂዷል።

‎በጉባኤው የ2018 በጀት ዓመት የ3ኛ ሩብ ዓመት የሥራ አፈጻጸም ሪፖርት ቀርቦ ውይይት ተደርጎበታል።

‎መድረኩን በንግግር የከፈቱት የኮቾሬ ወረዳ ምክር ቤት አፈ ጉባዔ አቶ አለሙ መንገሻ፤ በወረዳው ህዝብ የሚያነሳቸውን የልማት፣ የዕድገት፣ የመልካም አስተዳደርና ፍትሐዊ የአገልግሎት አሰጣጥ ጥያቄዎችን ለመመለስ የምክር ቤቱ አባላት በታማኝነት፣ በቁርጠኝነትና በተነሳሽነት መሥራት እንደሚገባቸው ተናግረዋል።

‎አፈ ጉባኤው አያይዘውም የግብርና ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ በዘንድሮው የምርት ዘመን በሁሉም አካባቢዎች በሕብረተሰቡ ዘንድ ንቅናቄ በመፍጠር በተከናወኑ ተግባራት ተጨባጭ ውጤቶች መመዝገባቸውንም አስገንዝበዋል።

‎የኮቾሬ ወረዳ አስተዳዳሪ ዶክተር ዳዊት ጀቦ የወረዳ አስተዳደሩን ሪፖርት ባቀረቡበት ወቅት እንዳብራሩት፤ በተጠናቀቀው በጀት ዓመት በግብርናው ዘርፍ በእንሰሳት ርባታ፣ በንብ ማነብ፣ በሥራ ዕድል ፈጠራ፣ በእንሰት ልማት ኢኒሼቲቭ፣ በግብርናና በገቢ አሰባሰብ የተሻለ አፈጻጸም ተመዝግቧል።

‎የመልካአላቲ ድልድይ ግንባታ ሥራ በአሁኑ ሰዓት አፈጻጸሙ 95 በመቶ መድረሱን ገልፀው፤ ሁለንተናዊ ዕድገት በማፋጠን ቀጣይነት ያለውን የሕዝቡን የልማት ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ በመንግሥት የተጀመሩ ተግባራዊ እንቅስቃሴዎችን ከዳር ለማድረስ እየተሠራ እንደሚገኝም ነው የገለጹት።

‎በአሁኑ ሰዓት በተለያዩ ቀበሌያት የ15 ኪሎ ሜትር የመንገድ ከፈታ ሥራዎች ከመሠራታቸውም በላይ በቂ ድጋፍና ክትትል እየተደረገ እንደሚገኝ አስታውሰዋል።

‎አያይዘውም በመብራት ኃይል መቆራረጥ፣ በንፁህ የመጠጥ ውሃ አቅርቦት፣ በመድኃኒት እጥረት፣ በአንዳንድ የሕክምና መገልገያ ቁሳቁስ እጥረት በዘርፉ እንደ ችግሮች የተገመገሙ ጉዳዮች መሆናቸውን ገልፀው በቀጣዩ በጀት ዓመት ከሚመለከታቸው መዋቅሮች ጋር ምላሽ ለመስጠት እየተመካከሩ መሆናቸውንም አንስተዋል።

‎በቅርቡ ተመርቀው ወደሥራ የገቡ የኮሪደር ልማት ሥራዎች፣ የንጹህ መጠጥ ውሃ ፕሮጀክቶችና ልዩ ልዩ የመንገድ መሠረተ ልማት ሥራዎች በወረዳው የተተገበሩ የመልካም አስተዳደር ውጤቶች መሆናቸውን የጠቆሙት አስተዳዳሪው፤ ለሕብረተሰቡ ልማት የተገዙ ግሬደር ማሽኖችን በቅርቡ ለማስመረቅ እንቅስቃሴ ላይ እንገኛለን ሲሉም አክለዋል።

‎ከፍስሐገነት ጨለለቅቱ መንገድ ለረጅም ጊዜ በሕዝቡ ዘንድ ጥያቄ ይነሳበት የነበረና አስፈላጊው ጥገና በወቅቱ ባለመደረጉ በዕለት ተዕለት የሥራ እንቅስቃሴ ላይ ጫና ሲፈጥር እንደቆየ ጠቁመው ከዞን፣ ከክልልና ከፌዴራል መንግስት ጋር በመናበብ ምላሽ ለመስጠት እየሠሩበት እንደሚገኝም ተናግረዋል።

‎የመድረኩ ተሳታፊዎች በሰጡት አስተያየት በጤናው አገልግሎት አሰጣጥ በተለይም በማዐጤመ አተገባበር ዘርፍ በወረዳው የተሻለ አፈጻጸም እንዳስመዘገበው አንስተው ቀሪውንም ተግባር በአዲሱ የሥራ ዘመን በዕቅዱ አካቶ ማሳካት ያስፈልጋል ብለዋል።

‎ዘጋቢ: እስራኤል ብርሃኑ – ከይርጋጨፌ ጣቢያችን